Sunday, November 18, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል አንድ


                                                                                                        በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡
ሐሳቡን በትክክል ለመያዝና ለማጥናት እንዲረዳን የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡ 
1ኛ. መቆም:- መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡
ለዚህ ሁሉ አገባብ ማስረጃ ብትሻ እነዚህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በሚገባ ፈትሽ፡፡ ‹‹የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ›.፣ ‹‹የደመናው ዓምድ ቆመ››፣ ‹‹በሃይማኖት ቁሙ›› (ሉቃ8.44፤ ዘዳ31.15፤ ዘኁ10.12፤ 1ቆሮ16.13) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መቆም የሚለው ቃል የተለያየ ሐሳብ ይዞ መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡
አሁን ከዚህ ቦታ ከርእሳችን አንጻር እኛ የምንፈልገው ቆመ የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም ይዞ መገኘቱን መረዳት ነው፡፡ መቆም ሲባል ማማለድ የሚል ትርጓሜ እንዳለው ለመረዳት ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተጻፈውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እስራኤላውያን ጣዖት በማምላክ ፈጣሪቸውን አስቆጡት፡፡ እርሱም ሊያጠፋቸው ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሙሴ እነዚህን ሕዝቦች ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስኝ በማለት በራሱ ፈርዶ አማለዳቸው፡፡ ፈጣሪም የሙሴን ልመና ሰምቶ መዓቱን በትዕግሥት መለሰ፡፡ ይህ ታሪክ በዘፀአት የኦሪት ክፍል ተመዝግቧል፡፡ (ዘፀ32.32)


ይህንን የሙሴ ምልጃ ቅዱስ ዳዊት በሌላ ጊዜ በድጋሚ ተርኮታል፡፡ ይኸውም በዳዊት መዝሙር የምናገኘው ነው፡፡ ነገር ግን አተራረኩ መቆም ማማለድ መሆኑን በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፡፡ እንዳያጠፋቸው ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ፡፡›› የተሰመረበትንና ደምቆ የተጻፈውን ኃይለ ቃል ልብ ብለህ ተመልከት፡፡ (መዝ015.23) ባይቆም ኖሮ ሲል ባያማልዳቸው፣ ባይለምንላቸው፣ ባይጸልይላቸው ኖሮ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ መቆም የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም እንደሚኖረው እንረዳለን፡፡


ዳግመኛም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች (መላእክት) በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፡፡ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ›› ይለናል፡፡ ‹‹ለመቆም›› ሲል ለመለመን፣ ለማማለድ ማለት ነው፡፡ አብሮአቸውም ሰይጣን መምጣቱን ልብ በል፡፡ ሰይጣን የመጣው ለምን ነበር? ጻድቁ ኢዮብን ለመፈተን ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ፈጣሪውን ለመለመን አልነበረምን? የመላእክትም አመጣጥ ፈጣሪቸውን ስለሰው ለመለመን እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ ይህን ሲገልጥ ‹‹ለመቆም መጡ›› ይለናል፡፡ መቆም መለመን፣ ማማለድ ማለት ነውና፡፡ (ኢዮ1.6)
መቆም ማለት መጸለይ፣ ማማለድ የሚል ፍቺ እንዳለው ካስጨበጡ በኋላ ይህንን ቃል በመጠቀም የመላእክትን አማላጅነት ማስረዳት ቀላል ይሆናል፡፡
ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛ ከምናውቀው ውጭ አንዳንድ ጊዜ በተቃራኒ አቅጣጫም እንኳን ፍቺ ይዘው ይገኛሉ፡፡ አገባባቸውን እንደመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤና ምሥጢር መማር የሚያስፈልገው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ለብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ ቃላትን ትክክለኛ መንፈስ አለመረዳት የመላእክትን አማላጅነት እንዳይረዱ አድርጓቸዋልና፡፡
ለምሳሌ፡- ቅዱስ ገብርኤል ራሱ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል የተጻፈ ኃይለ ቃል ሲሆን አብዛኞቻንን እናውቀዋለን፡፡ ልዩ የሚሆነው ግን የቃሉን ትክክለኛ አገባባዊ ትርጉም ባለማወቃችን ምክንያት መልአኩ ይህን ባለ ጊዜ ‹‹እኔ አማላጅ ነኝ›› እንዳለን አድርገን አለመረዳታችን ነው፡፡ መቆም ማለት ማማለድ የሚል ትርጉም ካለው ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የምቆም›› ማለት ደግሞ ‹‹የማማልድ›› ማለት መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነቱን ራሱ ግልጽ በሆነ መንገድ ነግሮናል ማለት ነው፡፡
እስኪ እናንተ ፍረዱ! በዚህ ስፍራ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅ ነኝ ማለቱን ካላመንን ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ማለቱን ምን ብለን እንረዳዋለን? የእግዚአብሔር ፊቱ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ነው እንጂ እንደፍጡር ወደ አንድ ገጽ የተወሰነ አይደለም፡፡ መላእክት ደግሞ በተፍጥሯቸው እንደ ሰው ልጅ የሚታጠፍና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ ስለሌላቸው አይቀመጡም፤ አይተኙምም፡፡ ታዲያ አማላጃችሁ ነኝ ማለቱ ካልሆነ በቀር መልአኩ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ሲል ምን ማለቱ ነው? መልአኩ እግዚአብሔርን እንደ ምድራዊ ንጉሥ ራሱን ደግሞ እንደ ንጉሥ ወታደር ቆጥሮ በንጉሡ ፊት ቀጥ ብዬ የምውል ዘበኛ ነኝ ማለቱ ነውን? በፍጹም አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ደጅ አፍ መቆምና በእግዚአብሔር ፊት መቆም ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምሥጢራቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ (ራእ21.12፤ ዘፍ3.24) ይልቅ ሊሆን የሚችለው እኔ በፊቱ ባለሟልነት ያለኝ ሁሉ ጊዜ ስለ እናንተ የማማልድ ነኝ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡


መልአኩ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ለምንድን ነው? ለማመስገን ነው እንዳንል ይህንን ሐሳብ ለካህኑ ለዘካርያስ መንገር ለምን አስፈለገው? የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ትርጉሙ እንዲህ ቢሆን ወደ ካህኑ ወደ ዘካርያስ ከመጣበት ጉዳይ ጋር ንግግሩ ምንም ግንኙነት አይኖረውምና ይህን መናገር አያስፈልገውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እኔ ሰዎችን ሁሉ ለማማለድ በእግዚአብሔር የምቆም ባለሟልነት ያለኝ መልአክ በመሆኔ የለመንከው ልመና መድረሱን የምሥራች ልነግርህ ብመጣ ቃሌን እንዴት ትጠራጠራለህ? ለማለት ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ›› በማለት መልአኩ ይህን ተናገረ ብንል ከሁሉ በላይ የሚያስኬድና ለአእምሮ የሚመች ትክክለኛ ትርጓሜ ነው፡፡


በተመሳሳይ መልኩ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም በትንቢተ ዳንኤል ላይ እንዲህ ተጽፏል፡፡ ‹‹በዚያ ወራት ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› ይላል፡፡ (ዳን12.1) በዚህ ጥቅስ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ተብሏል፡፡ እረ ለመሆኑ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ‹‹የሚቆመው›› ለምንድር ነው? ለማማለድ አይደለምን? ይህን ካልተቀበልን ቃሉን ምን ብለን እንተረጉመዋለን? ለማመስገን ይቆማል እንዳንል ቃሉ የሚለው ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ነው፡፡ ስለ እኛ ጥብቅና ይቆማል እንዳንል ወደ ባሰ ስሕተት ይወስደናል፡፡ ሚካኤል በእግዚአብሔር ፊት ጥብቅና አይቆምምና፡፡ እግዚአብሔርም በጠበቃ የሚሟገቱት አምላክ አይደለምና፡፡ ጥብቅና ይቆማል ከማለት ይልቅ ትክክለኛውና የሚስማማው ወደ ፈጣሪ ሊለምንልን ወይም እኛን ለማማለድ ይቆማል የሚለው ትርጓሜ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደተመለከትነው ‹‹መቆም›› የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም አለውና፡፡


ይህ ለምሳሌ ያህል ተጠቀሰ እንጂ በፈጣሪ ፊት እልፍ አእላፋት መላእክት ለምልጃ ይቆማሉ፡፡ ቅዱስ ዳንኤል ‹‹ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፡፡ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፡፡›› በማለት የገለጸው ይህንን እውነት ነው፡፡ (ዳን7.9-11)
ከዚህ በላይ ከብሉይ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከሐዲስ ደግሞ ስለ ቅዱስ ገብርኤል የተጻፉት ለማስረጃነት ተጠቅሰዋል፡፡ የተማሩትንና ያነበቡትን በልብ ለመክተብ መላልሶ ማንበብና ማጥናት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ብትሻ የቅዱስ ገብርኤል ዝክረ በዓል ወር በገባ በአሥራ ዘጠኝ እንደሚውል ታውቃለህ፡፡ ስለ እርሱም የተጠቀሰው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1.19 መሆኑን ልብ በልና ጥቅሱ ከወርኃዊ በዓሉ ጋር ያለውን ዝምድና መርምር፡፡ ማለትም ቁጥር 19 ላይ መጻፉን አስተውል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም እንዲሁ አድርግ፡፡ ጥቅሱ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ወርአዊ ክብረ በዓሉም በ12ኛው ቀን ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህንንና ይህን የመሰለ የራስህን የማጥኛ ዘዴ በመጠቀም ጥቅሶቹን በቃልህ ለማጥናት ሞክር፡፡

ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ

ጽንሰ ሐሳብ፡- መቆም ማማለድ ማለት ይሆናል፡፡ የዚህ ማስረጃው (መዝ105.23፤ ኢዮ1.6) ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ በፈጣሪ ፊት ይቆማሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡
በቃል የሚጠኑ ጥቅሶች
  • 1ኛ.ሉቃ1.19
  • 2ኛ.ዳን12.1
  • 3ኛ.ዳን7.9-11እነዚህን ማጥናት አያቅትምና አጥንቶ ለልጆች በማስጠናት የወላጅነት ግዴታችንን በዚህ መንገድ እንወጣ!
2ኛ. ማየት:- መቆም እንደሚለው ቃል ሁሉ ‹‹ማየት›› የሚለው ቃልም በመጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የሆነ አገባባዊ ፍቺ አለው፡፡ በዓይን መለማመጥ፣ ማሳዘን፣ መቆጣት፣ ተስፋ ማድረግ እና ማስፈራራት ይቻላል፡፡ ‹‹የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፡፡›› እንዲል፡፡ (መዝ 144.15) ስለዚህ ‹‹ማየት›› መመርመር ወይም ንስሐ መግባት፣ መለመን፣ መጸለይ፣ ተስፋ ማድረግ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ መቆጣት ወዘተ የሚሉ ፍቺዎች አሉት፡፡
በተለይ ከእግዚአብሔር አንጻር ካየነው ማየት የሚለው ቃል መስማት፣ መቀበል፣ ይቅር ማለት የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ "እግዚአብሔር እገሌን በዓይነ ምሕረት አየው" ማለት አሰበው፣ ጎበኘው፣ ማረው፣ ሰማው ፣ ይቅር አለው ማለት ይሆናል፡፡ እንደ አገባቡ ተቆጣው ማለትም ሊሆን ይችላል፡፡ ለጠቀስናቸው ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፡፡››፤ ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፡፡››፤ ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮውም ወደ ጩኸታቸው ነው፡፡›› የሚሉትን ማስረጃዎች መመልከት ብቻ እንኳን ይበቃል፡፡ (ዘፍ 4.4፤ መዝ 32.18፤ 33.15)
"ማየት" የሚለውን ቃል ከሰው አንጻር ወይም ከፍጥረት ሁሉ አንጻር ካየነው ደግሞ ሌሎች ፍቺዎች ይኖሩታል፡፡ ‹‹አቤቱ አምላኬ እየኝ ስማኝም፡፡›› ሲል ማረኝ ለማለት ነው፡፡ "ማየት" መመርመር ሲሆን ‹‹ራስህን ለካህን አሳይ›› ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ራስህን አስመርምር፣ ንስሐ ግባ ማለት ነው፡፡ (ማቴ8.4፤ መዝ12.3) በእንግሊዝኛውም ይህን የመሰለ ነገር አለ፡፡ ነጮቹ ሕክምና ላድርግ ወይም ልመርመር ለማለት ‹‹ሐኪሜን ልይ›› ይላሉ፡፡
ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ‹‹ማየት›› የሚለውን ቃል ትርጉም በትክክል በመረዳት የመላእክትን አማላጅነት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡


ለሰው ልጆች በሙሉ ለየራሳቸው ጠባቂ መላእክት አሏቸው፡፡ ይህንንም ያደረገው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና›› የሚለው የነቢዩ የዳዊት መዝሙር ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚጠብቋቸው መላእክትን እንዳዘጋጀ ያስረዳል፡፡ (መዝ90.11) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌያዊ ትምህርቱ ለበለሱ አትክልተኛ መቅጠሩ በበለስ ለተመሰሉ የሰው ልጆች ለእያንዳንዳቸው ጠባቂና ተንከባካቢ መልአክ ማዘጋጀቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ (ሉቃ13.6-9) በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ መልአኩ ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ (ዳን4.13፤ 4.23) በተጨማሪም ለሰው ልጆች ሁሉ ጠባቂ መልአክ እንዳላቸው በወንጌል ‹‹መላእክቶቻቸው›› በሚል የተቀመጠው ቃል ብቻ ምስክር ነው፡፡ (ማቴ18.10)
መላእክት እንደ ታላላቅ ወንድሞቻችን የምንቆጥራቸው እነርሱም ደግሞ እኛን እንደ ታናናሽ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው የሚያዩን ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ እነርሱ ከእኛ በፊት በዕለተ እሑድ የተፈጠሩ የአምላክ ልጆች ሲሆኑ እኛ ደግሞ በዕለተ ዐርብ የተፈጠርን የእግዚአብሐር ልጆች ነንና፡፡ (ኢዮ1.6፤ 2.1፤ ዮሐ1.12) የአንድ አባት ልጆች ደግሞ ወንድሜ እኅቴ እንደሚባባሉ የታመነ ነው፡፡ ስለዚህ መላእክት እየሳሱ ይጠብቁናልና እኛ የእነርሱ ገንዘብ ነን፡፡ እነርሱም የእኛ ገንዘቦች በመሆናቸው ‹‹መላእክቶቻቸው›› ተብለዋል፡፡ ይህም ከወንጌሉ ትረካ የምናታገነው ነው እንጂ በብልሃት የተፈጠረ ቃል አይደለም፡፡

እነዚህ ጠባቂ መላእክት ስለ ሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያዩ ወንጌል ይናገራል፡፡ ‹‹መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉና›› እንዲል፡፡ (ማቴ18.10) ይህም ዐረፍተ ነገር ያለ ምንም ጥርጥር የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ማየት መጸለይ ማማለድ የሚል ትርጉም እንዳለው ቀደም ሲል በሚገባ ተቀምጧልና፡፡ ካልሆነ ግን በምን ሊተረጎም ይችላል? የጥቅሱን ሙሉ ሐሳብ ስንወስድ ሰዎችን አትናቁ! የምትንቋቸውን ሰዎች የሚጠብቁ መላእክት ዘወትር የአባቴን ፊት ያያሉ የሚል ነው፡፡ ይህም ለተናቁት ሰዎች ለምነው ያማልዷቸዋል፡፡ የምትንቁትን እናንተን ደግሞ ጸልየው ያስፈርዱባችኋል የሚል ማስጠንቀቀቂያ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ

ጽንሰ ሐሳብ፡- "ማየት" መጸለይ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ ይቅርታ ማድረግ ማለት ይሆናል፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ የፈጣሪን ፊት ያያሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡
በቃል የሚጠኑ ጥቅሶች
1ኛ. "ማየት" መስማት፣ መቀበል ሲሆን በፈጣሪ አንጻር
(ዘፍ4.4፤ መዝ32.18፤ 33.15)
2ኛ."ማየት" መጸለይ፣ ማማለድና ይቅርታ መጠየቅ ሲሆን ከፍጡር አንጻር
(ማቴ18.10፤ ማቴ8.4፤ መዝ12.3)

ይቀጥላል

4 comments:

  1. በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ kale hywet yasemaln, amen.

    ReplyDelete

  2. Kale Heywet Yasemalen Egzeabehare Edema Tsega Yestelen

    ReplyDelete

  3. Kale heywet yasemalen Egzeabehare Edema Tsega Beraket yestelen

    ReplyDelete