Sunday, November 18, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል ሁለት

                                                                                                                        በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡

“ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” /ሉቃ13.6-9/ይህን ቃል ጽፎ ያቆየልን ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ቢሆንም ትምህርቱን ያስተማረው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ይህንም ምሳሌ አለ›› ብሎ ታሪኩን በመጀመሩ ትምህርቱ ምሳሌያዊ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡

የበለሲቱ ጌታ /ባለቤት/ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ቢፈልግባት ምንም ስላላገኘባት እንድትቆረጥ ለሠራተኛው ጥብቅ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ሠራተኛው በፍጥነት ሊቆርጣት ይችል ነበር፡፡ ያን ቢያደርግም በጌታው ዘንድ  ሊመሰገን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የታዘዘውን አድርጓልና፡፡

ነገር ግን ጌታውን ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› በማለት ስለ በለሲቱ ለመነላት፡፡ አማለዳት ማለት ነው፡፡ ለሌላ ወገን የሚደረግ ልመና ምልጃ ነውና፡፡ የሚገርመው ደግሞ በለሲቱ እንዲለምንላት አልተማጸነችም፡፡ ሠራተኛው በራሱ ደግነት በፈቃዱ ተነሣስቶ ለመነላት እንጂ፡፡ ብትለምነው ደግሞ የበለጠ ሊያደርግ እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡ ሊያማልድ ያልተዘጋጀ ወይም ያላሰብ ሰው እንኳን እባክህ አማልደን ብለው ሲልኩት እምቢ እንደማይል ሁሉ ይህ ሠራተኛ ቢለመን የበለጠ ሊያደርግ መቻሉ እሙን ነው፡፡

የበለሲቱም ጌታ የቀጠርኩህ እንድትታዘዘኝ እንጂ እንድትለምነኝ አይደለም ሳይል የሠራተኛውን ምልጃ ተቀበለ፡፡ ይህም ምልጃ ተቀባይ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡

ምሳሌው እንዴት እንደሚተረጎም እንመልከት፡- የበለሷ ጌታ /ባለቤት/ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ በለሲቱ ደግሞ እስራእላውያንን ቀጥሎም የሰውን ዘር በሙሉ ያመለክታል፡፡ ሠራተኛ የተባለውም ሰውን የሚጠብቅ መልአክ /ዑቃቢ መልአክ/ ነው፡፡ ከበለሲቱ በተስፋ የተጠበቀው ፍሬ ደግሞ ከሰው ዘር በሙሉ ፈጣሪ የሚፈልገው የቀና ሃይማኖትና መልካም ምግባርን ነው፡፡ ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ማጣቱ ፈጣሪ በታዳጊነት፣ በወጣትነትና በጎልማስነት ጊዜ ሁሉ ፍሬ እንደሚፈልግብን ያሳያል፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ማለቱ ፍሬ ሲያጣብን ያለ ዕድሜም መቀሠፍ እንዳለና ሞት እንደሚፈረድብን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሠራተኛ ለበለሲቱ እንደለመነላት መላእክትም ለእኛ እንደሚለምኑልን እንደሚያማልዱን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን መመልከት አለብን፡፡ ይህን ካልተቀበልን ምን ብለን ልንተረጉመው ነው? ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የሚባል መልአክ መሆ
ብቁንም ያዘዛቸው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል፡፡›› ተብሏልና፡፡ /መዝ90.11/ኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዳን4.13፤4.23/ እንዲጠ
ይህ ምሳሌያዊ ትምህርት በርካታ መልእክቶችን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ቃልና ዐረፍተ ነገርም ብዙ ምሥጢር ይዟል፡፡ የእኛ ርእስ ግን ስለ ምልጃ ስለሆነ በዚህ እንወሰናለን፡፡ ይሁን እንጂ ጎላ ያለ ጥያቄ መልሶ ለማለፍ ያህል አንድ ሰው የበለሲቱ ባለቤት ‹‹ትቆረጥ›› ሲል ሠራተኛው ደግሞ ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› ማለቱ ለበለሲቱ ከባለቤቱ ይልቅ ሠራተኛው ያዘነላት አያስመስልም? ሊል ይችላል፡፡
ለበለሲቱ ከሠራተኛው ይልቅ ያዘነላት ጌታዋ ነው እንጂ ሠራተኛው አይደለም፡፡ እንዴት ቢባል ጌታዋ ከአንድም ሦስት ጊዜ ሳይቆርጣት አልፎአታል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኛው የለመነላት ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲያው ከዚያ በኋላ ካላፈራች ‹‹ትቆርጣታለህ›› ሲል ተናገረ፡፡ ጌታዋ ለሦስት ጊዜ የታገሣትን እርሱ ግን አንዴ ከለመነላት በኋላ ብትቆረጥም ቅር እንደማይለው አስረዳ፡፡ ታዲያ ከጌታዋ ይልቅ እርሱ ራራ ለማለት እንዴት ይቻላል? በዚያውም ላይ ያ ሠራተኛ ቢለምንላትም ይቅር ያላት ግን ጌታዋ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር እንዲህ አዝኖ የሚያማልዳትን ሠራተኛ ያዘዘላት እኮ ጌታዋ ነው፡፡ በመጨረሻ ትምህርቱ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ያለው ጌታዋ የፈጣሪ ምሳሌ እንደመሆኑ መጠን ሠራተኛው የሚያቀርብለትን የምልጃ ጥያቄ አስቀድሞ ያውቃልና በለሲቱ እንደማትቆረጥ ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ በበለሲቷ ላይ ያለውን የማዘዝ ሙሉ ሥልጣን እና የሠራተኛውን ማለትም የጠባቂ መልአኩን የማማለድ ሥራ ሊያሳይ በሚችል መንገድ ምሳሌውን እርሱ ባወቀ መስሎ ተናገረ፡፡
  • -          በቃል የሚጠና ጥቅስ ሉቃ 13.6-9
  • -          ሐሳብ - የበለሲቷ ምሳሌ
  • -          ትምህርት - በሠራተኛው ልመና አንጻር የመላእክትን አማላጅነት ማሳየት
 የትምህርቱ ፍሰት ከከባድ ወደ ቀላል

ሀ. ማስታረቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን የሚክድ ካለም ‹‹የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሰን አፉን እናሲዘዋለን፡፡ (2ቆሮ5.18) መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ይህን ሲያስረዳ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ ‹‹መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፤ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል›› እያለ ሲጠቅሳቸው በሌላ ስፍራ ደግሞ ‹‹ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?›› ይላቸዋል፡፡ (መዝ103.4፤ዕብ1.14) ስለዚህ ማገልገል ማስታረቅን የሚያካትት ከሆነ መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ከሆኑ አስታራቂዎች /አማላጆች/ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ነገረን ማለት ነው፡፡
ለ. ይህም ብቻ አይደለም! ዕጣን በጸሎት ይመሰላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ›› ይላልና፡፡ (መዝ140.2) እንዲህ ከሆነ ‹‹ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።›› ይላልና፡፡ (ራእ8.3) በዚህ ጥቅስ መሠረት የእግዚአብሔር መልአክ የቅዱሳንን /የምእመናንን/ ጸሎት በዕጣን አምሳል እንደሚያሳርግ ከተረዳን አማላጅነቱን አወቅን ማለት ነው፡፡ አንድ መልአከ ጸሎታችንን ቅድመ እግዚአብሔር የሚያደርስ ከሆነ አማለደ ከማለት ውጭ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ያማልዱናል ማለት ልመናችንን ወደ እግዚአብሔር ያደርሱልናል ማለት አይደለምን?
ሐ. እስራኤላውያን በባቢሎን ምርኮ ለበርካታ አመታት በተሰቃዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ እነርሱ በግልጽ ቃል ምልጃ አቅርቧል፡፡ ይህም ምልጃው በዚህ መልኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቧል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ።›› (ዘካ1.12) መልአኩ ይህን ልመና ባቀረበ ጊዜ ‹‹እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።›› ይላል፡፡ (ዘካ1.13)
ታሪኩን ልብ ብሎ ያነበበ ሰው ይህ ‹‹መልካምና የሚያጽናና ቃል›› ምን ይሆን? ማለቱ አይቀርም፡፡ መቼም ‹‹የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?›› ለሚለው የልመና ቃል ‹‹ምሬአቸዋለሁ ወይም እምራቸዋለሁ›› ከሚል ውጭ የሚያጽናና ቃል ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም በግምት የቀረበ ሐሳብ ሳይሆን መልአኩ ለዘካርያስ ባስተላለፈው የመጨረሻ ቃል ይታወቃል፡፡ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ ቤቴ ይሠራባታል በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል።›› ብለህ ስበክ ብሎ ልኮታል፡፡ (ዘካ1.16-17
መልአኩ የለመነው ምን ነበር? ምሕረት አልነበርምን? ፈጣሪ ደግሞ በምሕረት ተመልሻለሁ ሲል መለሰ፡፡ የመልአኩ አማላጅነት ተቀባይነት አግኝቷ ማለት ነው፡፡ መላእክት ያማልዳሉ ስንል ይህን የመሳሰሉ ጠንካራና በርካታ መረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አግኝተን ነው እንጂ ከራሳችን ፍላጎት ተነሥተን አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ይህን ጥቅስ በተመለከተ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ አንድ ቀን ከአንድ መናፍቅ ጋር በአጋጣሚ የሃይማኖት ጉዳይ ተነሣና መነጋገር ጀመርን፡፡ ርእሱም ስለመላእክት አማላጅነት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ለማስረዳት ይህን ጥቅስ ጠቀስኩለት፡፡ ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹መላአኩ እኮ የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ እንጂ አልለመነላቸውም፤ ማራቸውም አላለም፡›› ብሎኝ እርፍ፡፡ እኔም እሺ ታዲያ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አልኩት፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹መቼ ልትምራቸው አስበሃል? ብሎ ቀጠሮ ነው የጠየቀው›› ሲል ደመደመ፡፡ ምንም እንኳን የምንማረው ለመናፍቃን መልስ ለመስጠት ብለን ባይሆንም እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ድርቅና ሊያጋጥማችሁም እንደሚችል አትርሱ፡፡
እንደዚህ መናፍቅ አተረጓጎም መልአኩ የጠየቀው ‹‹እስከ መቼ›› ብሎ ቀጠሮ ከሆነ መልሱ ‹‹በዚህ ጊዜ›› የሚል እንጂ ‹‹በምሕረት ተመልሻለሁ›› የሚል አይሆንም ነበር፡፡ ጥያቄው ምን እንደነበር ከመልሱ በመነሣት ማወቅ ይቻላል፡፡ ሌላው ቋንቋው አማርኛ እስከሆነ ድረስ በሌላም ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፡፡ አንድ አባት በማምሸትና በመስከር ያስቸገረውን ልጁን ‹‹ልጄ እንደዚህ የምትሆነው እስከመቼ ነው?›› ቢለው ቀነ ቀጠሮ ስጠኝ እንጂ አለው ብለን እንደማንፈታው የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሐረግ በስድሳ ስድስቱ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ከ50 ጊዜ በላይ ስለተጠቀሰ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ምሳሌውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስናደርገው ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ እስከመቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ?›› እያለ ሲጸልይ ቀን ቅጠርልኝ ማለቱ ሳይሆን አትርሳኝ እንጂ እያለ መለመኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ (መዝ12.1) ስለዚህ መልአኩም ‹‹የማትምራቸው እስከመቼ ነው?›› ሲል ‹‹ማራቸው እንጂ፤ አባክህ ማራቸው!›› እያለ እንደለመነላቸው ከምላሹም መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት በእውነት አማላጆቻችን ናቸው፡፡
 ንጽጽር
ማንም ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳ የሚችለው ነገር ሰይጣን በተፈጥሮው መልአክ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት››፤ ‹‹ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት››፣ ‹‹… የቀደመው እባብ ተጣለ:: ወደ ምድር ተጣለ :: መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡›› የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐረፍተ ነገሮች ምንም ግብራቸው ቢከፋ ሰይጣንና ሠራዊቱ ተፈጥሮአቸው መልአካዊ መሆኑን ያስረዱናል፡፡ (ይሁቁ.6፤ 2ጴጥ2.4፤ ራእ12.9)
ሰይጣን የሰው ልጆችን ይፈትናል፡፡ እንዲያውም ሰይጣን በቅዱስ ወንጌል ‹‹ፈታኝ›› ተብሏል፡፡ (ማቴ4.3) ይሁን እንጂ እንዳገኘው ደርሶ ሰዎችን የመፈተን መብት የለውም፡፡ ስለዚህ በሰዎች ላይ ላዘጋጀው ፈተና ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ምን ጊዜም ፈጣሪን ይለምናል፡፡ ፈጣሪም ማንንም ሰው በዓቅሙ እንጂ ከዚያ በላይ እንዳይፈትን መመሪያ ሰጥቶ ይፈቅድለታል፡፡ ይህንንም ጉዳይ የሥራ ወይም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለሥራ እንደ መሰማራት ልናየው እንችላለን፡፡
በዚህ መሠረት ሰይጣን ጻድቁ ኢዮብን ለመፈተን ሲያስብ ከመላእክት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ተገኝቶ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ (ኢዮ1.6-22) ይህን ሐሳብ በተመለከተ ሌላም የማያሻማ ቃል በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል፡፡ ‹‹ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥታችሁ ለመነ›› (ሉቃ22.31) አያችሁ! ይህ አሠራር አይለወጥም፡፡ ምእመናን! እኛ ባንረዳው ነው እንጂ ሰይጣን የሰው ልጆችን ሁሉ የሚፈትው ዘወትር በዚህ መንገድ እያለፈ ነው፡፡ አስቀድሞ ይለምናል ከዚያ በኋላ ባገኘው ፈቃድ መሠረት ይፈትነናል፡፡ ከምንችለው በላይ እንፈተን ዘንድ የማይፈቅድ ልዑለ ባሕርይ አምላካችን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!
ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስ፡፡ በዚህ ክፍል የጀመርነው ትምህርት የመላእክትን አማላጅነት ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ተግባር ጋር እያነጻጸሩ ማየት ነው፡፡
ሰይጣን ክፉ መልአክ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔርን እየለመነ እኛን ለመጉዳት የሚፈትነን ከሆነ ቅዱሳን መላእክት እኛን ከክፉ ነገር ሁሉ ለማዳን፣ ለመርዳትና ለመጥቀም ፈጣሪን አይለምኑትምን? ከለመኑትስ አማለዱ ማለት አይደለምን? እነርሱ ስለኛ ፈጣሪን የማይለምኑ ከሆነ የሰይጣንን ያህል ለተልኮአቸው አይተጉም ያሰኛል፡፡ ቅዱሳን መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው ሳለ እንደ ታናናሽ ወንድሞቻቸው የምንቆጠርና እንደ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን እኛ ክርስቲያኖችን ለማዳን ፈጣሪን የማይለምኑት ከሆነ ከሚጎዳን ከሰይጣን በምን ይሻሉናል?
በዚህም ላይ ፈጣሪስ ቢሆን  እኛን ለመጉዳት እንዲለምነው ለሰይጣን ዕድል ሰጥቶት ቅዱሳን መላእክት ግን እንዳይለምኑት የሚቃወማቸው ይመስላችኋልን? ከክፉ ይልቅ በመልካም ነገር ደስ የሚሰኘው ልዑል አምላክ እንዲህ ሚዛኑን የሳተ ፈቃድ እንደሌለው እኛ ክርስቲያኖች ፈጽመን እናምናለን፡፡ ስለሆነም መላእክት በእውነት አማላጆቻችን ናቸው! እያልን ስንመሰክር እንኖራለን፡፡ አሜን!
ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ
ጽንሰ ሐሳብ፡- ሰይጣን መልአክ ነው፡፡ እርሱ ሰዎችን ለመፈተን ፈጣሪውን እንደሚለምን እስከታመነ ድረስ መላእክት የማያማልዱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሰይጣን ሰውን ለመጉዳት ቅዱሳን መላእክት ደግሞ ሰውን ለመጥቀም እግዚአብሔርን ይለምኑታል፡፡
1ኛ. ሰይጣን መልአክ ነው፡፡
          (ይሁዳ ቁ6፤ 2ጴጥ2.4፤ ራእ12.9)

2ኛ. ሰውን ለመፈተን ፈጣሪን ይለምናል፡፡
                (ኢዮ1.6-22፤ ሉቃ22.31)

ይቆየን! 
 ሌሎች ጽሁፎች እና የምስል ወድምፅ ገፆች

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል አንድ
መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት ስሕተት ነውን?
የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነትና አማላጅነት

1 comment: