Tuesday, October 9, 2012

“የሚያየኝን አየሁት”

የክረምት ብርድ በተለያየ ምክንያት ከቤቱ የወጣውን መንገደኛ ፊት አጨፍግጎታል፡፡ ሰጥ አርጋቸው ደርጉም ከቡድኖቹ ጋር የዕለት እንጀራውን ለመጋገር ታክሲ ውስጥ ገብቷል፡፡ እሱም ሆነ ጓደኞቹ የማውራት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሌሊት በእርሱ አጠራር “ግዳጅ” የሚሉት የተደራጀ የሌብነት ሥራ ሲሠሩ ስላደሩ እንቅልፍ በማጣት ዐይኖቻቸው ቀልተው አብጠዋል፡፡ የወረዛው የታክሲው መስታወት ላይ የእነሱ ትንፋሽ ተጨምሮበት በጉም ውስጥ የሚሔዱ አስመሰላቸው፡፡
“ወራጅ” አለ፤ ሰጥ አርጋቸው፤ መስታወቱን በእጁ ጠረግ ጠረግ አድርጎ ወደ ውጭ እየተመለከተ፡፡ እጁ ላይ ውፍረቱ እጅግ የሚደንቅ የወርቅ ካቴና አድርጓል፡፡ ባለታክሲው ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበው ሕዝብ ግርግር ስለፈጠረበት አለፍ አድርጎ አወረዳቸው፡፡ ስድስት ወንዶችና ሁለት ነጠላ መስቀለኛ ያጣፉ ሴቶች እንደኮማንደር በየተራ ዱብ ዱብ አሉና ሰጥ አርጋቸውን ከበቡት፡፡ 

“ሄይ! ጊዜ አናጥፋ፤ ባለፈው ዓመት እንዳደረግነው ቶሎ ቶሎ ሒሳባችንን ዘግተን ውልቅ፡፡” ሲል፤ አንደኛዋ ሴት “አዎ በእናታችሁ መታ መታ እናድርግና ከዚህ እንጥፋ፤ ዛሬ የምንቅመው ጫት መቼም…” ስትል የቡድኑ መሪ አቋረጣትና “ዲሞትፈርሽን ይዘሻል?” አላት፡፡ በነጠላዋ ደብቃ ስለቷ የበዛ ትንሽ ምላጭ በኩራት አሳየችው፡፡ “በቃ እኔ አምና ከቆምኩበት ከመቃብር ቤቱ ጎን እቆማለሁ፡፡ ዕቃ ከበዛባችሁ እያመጣችሁ አስቀምጡ፡፡ የቡድናችንን ሕግ በየትኛውም ደቂቃ እንዳትረሱ፡፡” አላቸው፡፡ ሕጉ ከመካከላቸው አንድ ሰው ቀን ጥሎት ቢያዝ፤ ብቻውን ይወጣዋል፡፡ ስለቡድኑ መረጃ ከመስጠት ይልቅ አንገቱን ለሰይፍ ቢሰጥ ይመርጣል፡፡ 


ሰጥ አርጋቸው ረጋ ባለ ድምፅ “ዳይ… ዳይ እግዚአብሔር ይርዳን” ሲላቸው ሁሉም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እግራቸውን አፈጠኑ፡፡ እሱም ከኋላቸው የጨዋ መልክ ተላብሶ ተከተላቸው፡፡ የእጁን ካቴና፣ የአንገቱን ገመድ መሳይ ሀብል ያየ ሁሉ ለእሱ በመስጋት ያዩታል፡፡ ሐሳባቸውን ቢረዳ “ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምን ይደንቀው” የሚለውን ተረት ይተርትባቸው ነበር፡፡ 

ቅዳሴው አልቶ ታቦት እየወጣ ነው፡፡ እልልታው ይቀልጣል፡፡ ወንዶች ፊታቸውን አብርተው ወደ መድረኩ ቁመታቸው በፈቀደላቸው መጠን እያዩ እጃቸው እስኪቃጠል ያጨበጭባሉ፡፡

ሰጥአርጋቸው እግረ መንገዱን አንድ ዘመናዊ ሞባይል በተመስጦ በሚያጨበጭብ ወጣት ኪስ ውስጥ ሲያይ በተለመደው ፍጥነቱ ወስዶ ጓደኞቹን ወደ ቀጠረበት ቦታ ለመድረስ በሰው መሐል ይሹለከለካል፡፡
አሁን እልልታውና ጭብጨባው ጋብ ብሎ ለዕለቱ የሚስማማ ስብከተ ወንጌል እንዲያቀርቡ የተመደቡት ሊቀ ጠበብት መድረኩን ይዘውታል፡፡ 
    “…. ዛሬ እንደሚታወቀው የሁለቱ ዐበይት ሐዋርያት ክብረ በዓል ነው፡፡ ትምህርታችን ግልጥ እንዲሆንልን በወንጌል እጅግ ብዙ ፍሬ ከማፍራታቸው በፊት ስለነበራ    ቸው ሕይወት እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተቀመጠ ጊዜ “ጌታ ሆይ ሁሉም ቢክዱ እንኳን፤ እኔ ግን እስከመጨረሻው እከተልሃለሁ” ሲለው በራሱ እጅግ ተመክቶ ነበር፡፡ ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዶሮ ሳይጮኸ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡” አለው፡፡ ጴጥሮስ ተሟገተ፡፡ 
 
    “ነገር ግን ክርስቲያኖች ታሪኩን እንደምታውቁት የመጀመሪያውን አንዲት ሴትን ፈርቶ ካደ፡፡ እየቀጠለ ሦስት ጊዜ ሲክድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ የመከራ እጅ እንዳለ ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ የክርስቶስ እይታ እንደ መርፌ ወጋው፡፡ ባዶ ትምክህቱ ተገለጸለት፡፡ ከዛ ዘወር አለና አንጀቱ፣ ሆድ ዕቃው እሰኪናወጽ ይንሰቀሰቅ ገባ፡፡ ጌታ እንዳየው ጴጥሮስ ራሱን በራሱ ከሰሰ፡፡ እንባዎቹ እሳት ሆነው በጉንጮቹ ላይ ይጎርፉ ጀመር…” 
የሰጥ አርጋቸው ቡድን አባላት እየቀናቸው ነው፡፡ የአንገት ሀብል፣ የተቀንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎ፣ የገንዘብ ቦርሳዎች ሰብስበው ለዳግም ሙከራ ተሰማርተዋል፡፡ 

መምህሩ በተመስጦ ትምህርታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ “….ወዳጆቼ እኛንም እኮ በተለያየ ኃጢአት ውስጥ ስንመላለስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንና ምድርን የፈጠረ አባት የማያየን ይመስለን ይሆን? አንዳንዶቻችን  ፈጣሪ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ስለሚኖር፤ ይኼ የምናየው ሰማይ እግዚአብሔርን እንደመጋረጃ የሚጋርደው መሰለን እንዴ?...” እያሉ በሚስብ አንደበታቸው በተመስጦ ይናገራሉ፡፡ 

የሰጥአርጋቸው ጓደኞች እየተመላለሱ የሚያሲዙትን ዕቃ በትልቅ ጥቁር ፌስታል አቅፎ ቁጭ ባለበት ጆሮው የዐውደ ምሕረቱን ትምህርት እያመጣ ያቀብለዋል፡፡ ጆሮ ክዳን የለው፡፡ 

“…. ቅዱስ ጴጥሮስ ግን…..” ቀጥለዋል አባ፤
    “…. በፀፀት እንባው ኃጢአቱን ሁሉ አጠበ፡፡ ትርጉሙ “ሸንበቆ” የነበረ “ስምዖን” የተባለ ስሙን ጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ለውጦ ጴጥሮስ አለው፡፡ ጴጥሮስ ማለት “ዐለት” ማለት ነው፡፡እንደገናም ጌታችን ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ደጋግሞ አንድ ጥያቄ ጠየቀው “ጴጥሮስ ትወደኛለህን?” “አዎን ጌታ ሆይ” አለ፤ “ጴጥሮስ ትወደኛለህን” “አዎን ጌታ ሆይ” “ጴጥሮስ ትወደኛለህን” ሲለው ለሦስተኛ ጊዜ ጴጥሮስ አንዲት ኃይለ ቃል ተናገረ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ፡፡” አለው፡፡ በንስሐው ጊዜ ራስን ዝቅ ማድረግን ተምሯልና፡፡ እንደቀደመው ጊዜ በራሱ ትምክህት “እንዲህ አደርጋለሁ፤ እንዲህ እፈጥራለሁ” አላለም፡፡ በኋላም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ባደረገው ክርስቲያናዊ ተግባር ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር አሳየ የክርስቲያን ጠላቶች ሰቅለው ሊገድሉት በያዙት ጊዜም “እኔ እንደጌታዬ እንዴት እሰቀላለሁ? ራሴን ወደ ምድር ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ፡፡ በማለት እንደ ዐለት የጠነከረ እምነቱን ገለጸ፡፡ 
የሰባኪ ወንጌሉ ድምፅ ለአፍታ ተገታና መርሐ ግብር መሪው በእልህ መናገር ጀመረ፡፡ “….ምእመናን እባካችሁ ከሌቦች ራሳችሁን ጠብቁ በጣም ብዙ አቤቱታ እየደረሰን ነው፡፡ ሞባይል ስልኮች በሴቶች በኩል ቦርሳቸው በምላጭ እየተቀደደ እየተወሰደ ነው፡፡ ወንዶችም ኪሶቻችሁን ጠብቁ፡፡ በረት የገባው ሁሉ በግ አይደለም!” አለና ይቅርታ ጠይቆ ድምፅ ማጉያውን ለሊቀ ጠበብት ሰጣቸው፡፡ 

ሰጥ አርጋቸው የፕሮግራም መሪውን የእልህ ንግግር እየሰማ ፈገግ ለማለት ሞከረና አንዳች ነገር ሽምቅቅ አደረገው፡፡ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ተመለከተ፡፡ ሰማዩ እንደ ድሮው ነው፡፡ 
ሊቀ ጠበብት የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ማስተማር ቀጥለዋል፡፡ 
    “ሰማዕቱ ቅዱስ እሰጢፋኖስ ሲወገር ልብሳቸውን ከወጋሪዎቹ ጋር ተስማምቶ ይጠብቅ ነበር፡፡ ሴት ወንዱን እያስያዘ እስር ቤቶችን ሁሉ ሞላ፡፡ በኋላም የጠለቀ ክርስቲያኖችን ለመያዝ እንዲያመቸው የድጋፍ ደብዳቤ ለማምጣት ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ዳመና ጋረደውና “ሳ..ውል…ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?” አለው፡፡ በአምላካዊ ድምፅ ጌታ እኮ ሳውልን ማጥፋት ወይም መቅጣት አቅቶት አይደለም፡፡ ምስክር ሲሆነው ምርጥ ዕቃው አድርጎ መርጦታልና፡፡ 
 
    “ጌታ ሆይ አንተ ማን ነህ?” አለ ቅዱስ ጳዉሎስ ግራ ገብቶት 
 
    “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ አለው፡፡” “ተመልከቱ እንግዲህ” አሉ አባ እጅግ ተመስጠው፡፡ 
አንዳንድ እናቶች ከንፈራቸውን በተመስጦና በሐዘን ሲመጡ ከሚያሰሙት ድምፅ ሌላ ሁሉም በያለበት ቆሞ ጆሮውንና ልቡን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሥራ ላይ ከተሰማሩት የሰጥአርጋቸው ቡድኖች በቀር፤ “…. ቅዱስ ጳዉሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን እኮ በአካል አላገኘውም፡፡ ታዲያ እንዴት ለምን ታሳድደኛለህ አለው? ክርስቲያን ማለት በክርስቶስ ያመነ ማለት አይደለም ወገኖቼ? አይደለም ወይ?” ሲሉ ከፊት ያሉ ሕፃናት ድምፃቸውን ከሌሎች አጉልተው “ነው!” ብለው መለሱ፡፡ 
    “ሳውልም ያሳድድ የነበረው ክርስቲያኖችን ነበርና ነው፡፡ ዛሬ እኛም ስንቶችን አሳደድን ወገኖቼ! አሁን መርሐ ግብር መሪው የተናገረውን ሰምታችኋል አይደል? እዚህ መድረክ ላይ ብዙ ምእመናን ንብረታቸውን ተገፈው እያለቀሱ ነው፡፡ ማን ነው ከዚህ መሐል በክርስቲያኖች ላይ እጁን የዘረጋው? ዛሬም መድኃኔዓለም “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ? ቅዱስ ጳዉሎስስ የኦሪት ሊቅ ነበርና ማሳደዱ ስለ አምልኮቱ ቀንቶ እንጂ ስለ ሆዱ አልነበረም፡፡ እሱን ሦስት ቀን የዐይኖቹን ብርሃን በመጋረድ የቀጣ አምላክ እኛንማ እንዴት ባለ ጨለማ ይቀጣን ይሆን? እሱን አምነው በተሰበሰቡ ክርስቲያኖች ላይ ደክመው ያፈሩትን በመስረቅ በማታለል ልጆቹን እያሳደድን ነው፡፡ ይኽን ያደረክ ወንድሜ! ይኽን ያረግሽ እኅቴ ሆይ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለምን ታሳድጅኛለሽ? ይልሻል፣ ይልሃል፡፡…” 
ሲሉ ሰባኪው፤ ሰጥአርጋቸው እጆቹ መንቀጥቀጥ ጀምረዋል፡፡ ሊቀ ጠበብት በሰውኛ ባህርያቸው ሁሉንም እያዩ ያስተምራሉ፡፡ በእሳቸው አካል ላይ ግን ለሰጥአርጋቸው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐይኖች ታዩት፡፡ የተጨነቁ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ላካቸው፡፡ በዚያም የክርስቶስ ዐይን ነበር፡፡ ወደ መሬት አቀረቀረ በዚያም የክርስቶስ ዐይን ነበር፡፡ “ለካ እስከ ዛሬ ክርስቶስ ያየኝ ነበር፤ ያላየሁት እኔ ነኝ” አለ በልቡ፡፡ 

ሊቀጠበብት እንደቀጠሉ ነው “ወገኖቼ የእኛ አምላክ የቀደመውን በደላችንን ሳይሆን የኋላውን ብርታታችንን የሚመለከት ነውና፤ ቅዱስ ጳዉሎስ ጨርቁ እንኳን ድውያንን ይፈውስ ዘንድ እጅግ ብዙ ጸጋ በዛለት፡፡ ሐዋረያው ጳዉሎስም እውነት ለሆነው በፍፁም ፍቅር ሊጠራው ለእኛም ሳይገባው ቁስላችንን ለቆሰለልን፣ እሱ ታሞ ለፈወሰን፣ ተጠምቶ ላረካን፣ ተርቦ ላበላን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር አንገቱን በሰይፍ ተቆረጠ፡፡ ሰማዕትነትን በዚህች ቀን ተቀበለ፡፡ ዛሬ ሐምሌ አምስት ቀን የምናከብረው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ወገኖቼ እኛስ አንገታችንን የምንሰጠው ለማን ነው? ለዘላለም ሕይወት ለሚሰጠን ለአምላካችን ነው ወይስ በተንኮል ለሚተባበረን ባልንጀራችን? …” 

ሰጥአርጋቸው ጥቁሩን ፌስታል እንደያዘ ድንገት ብድግ አለና በሰዎች መሐል ወደ ፊት ይገሰግስ ጀመር፡፡ አንዱ ባልንጀራው ያገኘውን ይዞ ወደ እሱ ሲመጣ በሰው መሐል ሲሹለከለከ ያየውና “ለእኔ በጠቆመኝ ይሻል ነበር፡፡” እያለ በዐይኑ ይከተለዋል፡፡ የቡድናቸው መሪ ግን ግቡ ቅርብ አይመስልም፡፡ አሁንም በሰዎች መሐል ወደፊት እየተሹለከለከ ነው፡፡ 

ሊቀጠበብት እንደቀጠሉ ነው፡፡ “ቅዱስ ጳዉሎስ አሳዳጅ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ግን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱሱ ክርስቶስ ፍቅር በዝቶለት ልሔድ ከእርሱ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ..” እያለ በሙሉ ልቡ ይናገር የነበረው ስለ ስሙ ታስሮ ተገርፎ ተሰቃይቶ…” እያሉ ሲናገሩ አንድ ሰውነቱ ሞላ ያለ ወጣት እግራቸው ሥር ተንበርክኮ ከፌስታል ውስጥ ብዙ ቦርሳዎች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ወርቆች ዘረገፈ፡፡ 
ሊቀ ጠበብት ግራ ተጋብተው ወደ ልጁ ተጠጉና “ልጄ ሆይ! ምንድን ነው?” አሉት፡፡

ሰጥአርጋቸው አንገቱ ላይ ያለውን ወርቅ እየፈታ ቀና ብሎ አያቸው፡፡ እሳቸው ዐይን ውስጥ የኢየሱሱ ክርስቶስን ዐይን አየ፡፡ ዐይኖቹ በእንባ ተሞሉና በለሆሳስ “የሚያየኝን አየሁት” አላቸውና እግራቸው ሥር ተደፋ፡፡ 

ሊቀ ጠበብት በርከክ አሉና በፍቅር አቀፉት “ልጄ ስምህ ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ 

“ሰጥአርጋቸው” አለ አንገታቸው ውስጥ እንደተሸጎጠ፡፡ ሕዝቡ ገና ግራ በመጋባት ማጉረምረም ጀምሯል፡፡ ሊቀ ጠበብት በፍፁም ፍቅር ግንባሩን ሳሙና “እኔስ “ምሕረት” ብዬሀለሁ” አሉት፤ የእጁን የወርቅ ካቴና ሊያወልቅ ሲታገል እያገዙት እግዚአብሔር ይፍታህ ልጄ እግዚአብሔር ይፍታህ ይላሉ፤ ደጋግመው፡፡ 

/ምንጭ፦ ሐመር 17ኛ ዓመት ቁጥር 6 በትዕግሥት ታፈረ ሞላ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


6 comments: