Tuesday, October 30, 2012

ጸጋ ትኅትና

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡ 
ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ ያደረሱን “ፍቅረ መድኅን” የተሰኙ ተርጓሚ(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛ የግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን 113ኛ አበ አበው (ፓትርያርክ) እንደ ጻፉት) ሲሆኑ እኛም ጽሁፉ የያዘውን ቁመ ነገር ለእናነተም ልናካፍላችሁ ወደድን ተርጓሚውን አምላክ በእድሜ በፀጋ ይጠብቅልን፡፡ መልካም ንባብ፡፡                                                                                              ውርስ ትርጉም - በፍቅረ መድኅን
                                                                            የእንግሊዝኛው ርእስ- The Virtue of Humility
 እመቤታችን እና ንግሥታችን የምትኾን፤ የቅድስተ ቅዱሳን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን በዓል ምክንያት አድርገው    የመንፈሳውያን ዓርማ፤ የአጋንንት መውጊያ ስለኾነችው ስለ ትኅትና ቅዱሰነታቸው አቡነ ሲኖዳ ካስተማሩት

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን በዓል ምክንያት አድርገን ከታደለቻቸው ጸጋዎቿ አንዱ ስለኾነው ጸጋዋ እንነጋገራለን፡፡ይኸውም ትኅትና ነው፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወት ትኅትና ቀዳሚው ጸጋ ነው፡፡ትኅትና በመንፈሳዊ ሕይወት ግንባር ቀደም በመኾን ጸጋን እና ተሰጥዖን ይጠብቃል፡፡በትኅትና ያልታጀበ ወይንም ከትኅትና ጋር ያልኾነ ጸጋ ኹሉ በግብዝነት የተነሣ በሰይጣን ሊነጠቅ፤ በኩራት በመመካት እና ራስን በማድነቅ የተነሣ ሊጠፋ ይችላል፡፡
ወዳጄ: እግዚአብሔር ማንኛውንም ዓይነት ስጦታ ቢሰጥህ ከስጦታው ጋር ትኅትናን  ጨምሮ እንዲሰጥህ ካልኾነ ግን ካንተ እንዲወስድልህ ጸልይ፡፡ በተሰጠህ ስጦታ የተነሣ በመመካት እንዳትጠፋ፡፡

ትኅትና የሌሎች ጸጋዎች ኹሉ መሠረት ነው፡፡ጸጋዎች ኹሉ በትኅትና ላይ ያድጋሉ ወይንም ይገነባሉ፡፡ ትኅትና ለብቻው ተነጥሎ የሚኖር ጸጋ አይደለም፡፡ይልቁንስ በመቁጠሪያ ዶቃዎች ውስጥ እንደሚያልፍ እና ኹሉንም እንደሚያገናኝ ክር ነው፡፡
እግዚአብሔር የተለያዩ ስጦታዎቹን ለትኁታን ሰዎች ይሰጣል፡፡ ምክንያቱም እርሱ እነዚህ ስጦታዎች ተቀባዮቹን እንደማይጎዷቸው  ያውቃልና፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ  እግዚአብሔር ለትኁታን ሰዎች ምስጢሮቹን እንደሚገልጽላቸው እና የትኅትና ሕይወታቸው ባደገ መጠን ጸጋውንም እንደሚጨምርላቸው ይነግረናል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ትኁታን እንኾን ዘንድ ኹላችንን ይጠራናል፡፡ ክብር ይግባውና ፤ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በምድር ይመላልስ በነበረበት ወቅት ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሰዎች ኹሉ ዘንድ ተወዳጅ ካደረጉት ጠባያት ዋነኞቹ ትኅትናው እና የዋህነቱ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ወንጌልም ፡-በመንፈሱ የዋህ እና ትኁት ነበር፡፡ ሲል ይገልጸዋል፡፡
ቅዱሳን ትኅትናን በልዩ ኹኔታ ሲፈጽሙት ኖረዋል፡፡እነርሱ ትኅትናቸው በእግዚአብሔር እና በሰዎች ፊት ብቻ አልነበረም፡፡ በሰይጣናት ፊት ሳይቀር ትኁታን ነበሩ እንጂ፡፡ በዚህም የተነሣ ሰይጣናትን ድል አድርገዋል፡፡ ታላቁ ቅዱስ እንጦንስ ሰይጣናት በኃይል እና በቁጣ ኾነው ሲዋጉት በትኅትና እንዲህ እያለ ይመልስላቸው ነበር፡-ኃይለኞቹ እናንተ ፤ ከእናንተ መካከል ደካማ  ከኾነው ጋር እንኳን መዋጋት ከማልችል ከእኔ ከደካማው ሰው ምን አላችሁ?
ይኸው ቅዱስ ፡-አድነኝ ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ አድነኝ ፤ እኔ አመድ እና ትቢያ ስኾን የምረባና የምጠቅም ዋጋም ያለኝ  ከሚመስላቸው  አድነኝእያለ ወደ ፈጣሪው ሲጸልይ ሰይጣናት በሰሙት ጊዜ ከትኅትናው የተነሣ እንደ ጢስ በነው  እንደ ጉም ተነው ይጠፉ ነበር፡፡


አንድ ወቅት ሰይጣን ወደ ታላቁ መናኝ ወደ ቅዱስ መቃርስ መጣና እንዲህ አለው፡-ከአንተ የተነሣ ወዮልን ! ወዮታ አለብን  ኦ! መቃርስ ፤ አንተ ከምታደርገው እኛ የማንችለው ምን አለ አንተ ትጾማለህ ፤ እኛ ፈጽሞ አንበላም፡፡ አንተ በሌሊት ኹሉ ንቁ ነህ ፤ እኛ ግን አናንቀላፋም፡፡ አንተ በምድረ በዳ$ በበረሃ ትኖራለህ ፤ እኛም እንዳንተው በዚያ አለን፡፡ አንተ እኛን ድል ያደረግኸን በአንድ ነገር ነው፡፡”  ታላቁ ቅዱስም፡-ያ አንድ ነገር ያልኸው ምንድር ነው?ቢለው          መቃርስ፤ ድል ያደረግኸንማ በትኅትናህ  ነው፡፡ሲል ሰይጣን መልሶለታል፡፡
በሌላ ወቅት ደግሞ ቅዱስ እንጦንስ ሰውን ለማሰናከል በሰይጣናት የተጠመዱ ወጥመዶችን ተመለከተ ስለዚህም በእጅጉ አዝኖ  በእግዚአብሔር ፊት ራሱን አዋርዶ ሰውነቱን መሬት ላይ ጣለና አሰምቶ እያለቀሰ እንዲህ አለ፡- እግዚኦ ከነዚህ ወጥመዶች የሚድን ማነው?ይህን ተከትሎም እንዲህ የሚል ድምፅን ሰማ ፡-ከነዚህ የሚድኑ ትኁታን ሰዎች ናቸው፡፡
ሰይጣናትን እስከ ማሸነፍ ድረስ ኃይል ያለው ይህ 'ትኅትና ምንድር ነው?
ወዳጄ፤ ትኅትና የራስን ድክመት ማወቅ ፤ ውድቀትን እና ኃጢአትን መረዳት እንዲሁም እነዚህን እውነታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ራስን ማከም መቻል ነው፡፡ ትኅትና ማለት አንተ ታላቅ እንደኾንህ እየተሰማህ ታናሽ መስለህ ለመታየት የምትሞክርበት ወይንም ታላቅነትህን ለመደበቅ የምትጥርበት ኹኔታ አይደለም፡፡የታላቅነት ስሜት እየተሰማህ ከኾነ ይህ በግልጽ የሚያሳየው ትምክህትን ወይንም ኩራትን ነው፡፡ታላቅነትህን ለመደበቅ የምታደርገው ጥረትም መነሻው ራስህን ታላቅ አድርገህ መቁጠርህ ነው፡፡ ትክክለኛው  ትኅትና ግን መጀመሪያ ለራስህ በራስህ ፊት ትኁት መኾን ነው፡፡ማስመሰል በሌለበት ከልብ በመነጨ እና ነፍስን በዘለቀ ስሜት ደካማ እና ኃጢአተኛ የመኾህን እውነታ መቀበል ነው፡፡ለአንተ የጥንካሬ ጫፍ የምትለው ላይ የደረስክ ቢመስልህም እንኳ በእውነተኛ ትኅትና ውስጥ ካለህ ጥንካሬህ ከአንተ የተገኘ ሳይኾን ከእግዚአብሔር የተሰጠህ ሰማያዊ ስጦታ እንደኾነ ትገነዘባለህ፡፡
ወንድሜ ፤ ማን እንደኾንህ ማወቅ አለብህ፡፡ ምክንያቱም ማን መኾንህን የማወቅ እውቀት ወደ ትኅትና ይመራሃል፡፡ የተሠራኸው ከመሬት አፈር መኾኑን አስብ፡፡ አፈር እኮ ይቀድምኻል፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሔር ከአንተ አስቀድሞ ፈጥሮታልና፡፡ ከእርሱ'ከአፈርም  አንትን አበጀህ፡፡ እስቲ ከአንድ ግጥም ላይ የተወሰኑ ስንኞችን እነሆ፡-
             አንተ የመሬት አፈር ሆይ'    
              የሰው ልጆች ኹሉ አያት የምትሰኝ፡፡
              መነሻዬ ‘ ኮ  አንተ ነህ'
              አፈር ሆይ ፤ አዎ ከአዳምም ታረጃለህ'
              ሥጋዬም ወደ መቃብር ሲወርድ ዕጣ ፈንታዬም አንተ ነህ፡፡
ወንድሜ ፤ በትኅትና ኾነህ ካሰብኸው አንተ በእድሜ ልክህ እግዚአብሔርን በኃጢአቶችህ እንዳሳዘንኸው የመሬት አፈር ግን አላሳዘነውም፡፡አንድ በጣም ወሳኝ እውነታ ልንገርህ፡- ትኁት እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትልቅ ሲኾን ትንሽ ከምንኾን ከእኛ ጋር ለማውራት ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡እርሱ ፍጹም እና ቅዱስ ነው፡፡ ነገር ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ኃጢአተኛ ከምንኾን ከእኛ ከደካሞቹ ጋር ቃል ኪዳንን አደረገ፡፡ለእኛ ግን ትኅትናችን ራስን ዝቅ እንደ ማድረግ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም እኛ ትንሾች ነንና፡፡ትልቅ የኾነ እግዚአብሔር ግን በእውነት ትኁት ነውና ስለኛ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡
ወዳጄ ፤ ይህንን እውነት ካወቅህ ራስህን በተረዳኸው እውቀት በማጽናት ጠብቀው እንጂ ከሰዎች ክብርን እና ሞገስን አትፈልግ፡፡በዚህ የተነሣም ፈተና ከገጠመህ ለራስህ እንዲህ በለው፡-ከኃጢአቶቼ የተነሣ ለእኔ አንዳች ነገር አይገባኝም፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር በምህረቱ ብዛት ኃጢአቶቼን ከሰዎች ቢሸሽግልኝም  እኔ ግን ኃጢአቶቼን አውቃቸዋለሁ፡፡ ልረሳቸውም አይቻለኝም፡፡ ብመካም እንኳ በከንቱ እመካለሁ፡፡

ወዳጄ ፤ ኃጢአቶችህን  እንዳትረሳቸው ተጠንቀቅ፡፡ ምን አልባት ትዕቢት በልብህ ካለና ስለ ራስህ የተሳሳተ ልብ-ወለዳዊ አመለካከት አድሮብህ ከኾነ አንድ ቅዱስ የተናገረውን ማስታወስ ይጠቅማል፡፡ ቅዱሱ እንዲህ ነበር ያለው፡-                 ኃጢአቶቻችንን የምንረሳ ከኾነ እግዚአብሔር ያስታውሳቸዋል ኃጢአቶቻችንን የምናስታውስ ከኾነ ግን እግዚአብሔር ይተውልናል፡፡ ኃጢአቶችህን በራስህ'በእግዚአብሔር (በፈጣሪ እና በካህን ፊት) እና ከተቻለህም በሰዎች ፊት ተናዘዝ፡፡ በሰዎች ፊት ኃጢአቶችህን መናዘዝ ባትችል እንኳ በሌሎች ፊት ራስህን አታመስግን ፤ የሰዎችንም ምስጋና አትቀበል፡፡ ምስጋናቸውን ጆሮዎችህ ቢሰሟቸውም እንኳ ልብህ እና አእምሮህ ግን ለመስማት እምቢ ይበሉ፡፡
በእግዚአብሔርም ኾነ በሰዎች ፊት ለራስህ ክብር ወይንም ማዕረግ ለማግኘት አትሞክር፡፡ ቅዱስ ይስሐቅ የተናገረውን አስታውስ፡-ለራሱ ክብር ሲል ወደ ክብር የሚሮጥ ሰው ክብር ከእርሱ ሲሸሽ ይመለከታል፡፡ በዓላማ ክብርን የሚሸሻት ሰው ግን ክብር ስትከተለው ያገኛታል፡፡
ወዳጄ ፤ ትኅትናህ ለታይታ ወይንም በቃላት ብቻ አይኹን፡፡ ትኅትናህ ከእውነት'ከልብህ እና ከጥልቅ እምነት የመነጨ ይኹን፡፡ መንፈሳዊ ትኅትና፡፡
በትኅትና የምትኖር ከኾነ ሕይወትህ ኹልጊዜ የምስጋና ሕይወት ይኾናል፡፡ስለ ኹሉም ነገር በማንኛውም ኹኔታ ውስጥ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለህ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ኹልጊዜ ከሚገባህ በላይ እንዳደረገልህ የማወቅ እና የመረዳት ሕይወት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚኾነው ትኁት ያልኾነ ሰው የሚገባውን እንዳላገኘ እና ካለበት ኹኔታ የበለጠ ነገር ለእርሱ ይገባው እንደ ነበር በማሰብ በሰዎች እና በእግዚአብሔር እንደተጨቆነ አድርጎ ሲያጉረመርም እና ሲያማርር ይታያል፡፡
ትኁት ሰው ፤ ከሰው ኹሉ ጋር በሰላም ይኖራል፡፡ በማንም ሰው ላይ አይበሳጭምእርሱም ለሌሎች መበሳጨት ምክንያት አይኾንም፡፡ ትኁት ሰው በማንም ሰው ላይ የማይበሳጨው ኹልጊዜ ራሱን ስለሚወቅስ ነው፡፡ ማንንም የማያበሳጨውም የኹሉን ሰው ምርቃት ስለሚሻ ነው፡፡
የማይወሰን  እግዚአብሔር ራሱን ዝቅ አድርጎ እኛን እንደጎበኘን እና እንደተንከባከበን ፤ እስቲ ኹላችንም ትኁታን እንኹን፡፡ እግዚአብሔር በእኛ የሚሠራብን ለመኾን እንችል ዘንድ፡፡
ለዘለዓለም ለእርሱ ክብር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ፡፡ አሜን፡፡

1 comment: