Tuesday, September 18, 2012

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል አንድ



ቅዱስ ያሬድ ከአባቱ ከአብዩድ /ይስሐቅ/ ከእናቱ ከክርስቲና /ታውካልያ/ 505 .. ሚያዚያ 5 ቀን በአክሱም  ተወለደ፡፡ በዚህም መሰረት ታላቁ ቅዱስ ያሬድ በሚመጣው ሚያዝያ አምስት 1500 ዓመት ይሆነዋል ማለት ነው ፡፡ ታዲያ የዚህ ታላቅ አባት ለኢትዮጵያ እና ለቤተ ክርስቲያናችን ካበረከተው ታላቅ የአለም ሀብት አንፃር 1500ኛ አመቱ በታላቅ ድምቀት አመቱን ሙሉ መታሰብ ይኖርበታል ፡፡
መቼም ቢሆን እንዲት ሃገር የራሷ የሆነው ባህሏ / ሥርዓቷ/  የሚያኮራትና ማንነቷንም የሚያንጸባርቅ  በመሆኑ ልትጠብቀውና ከትወልድ ወደ ትውልድ ልታስተላልፈው የባለቤትነት ግዴታዋ ነው ፡፡ በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያን ለጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ እንድትሆን ያደረጋት የልጆቿ ሀገር ወዳድነትና ጀግንነትን የተመላው ባህሏ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፣ የሥነ ዜማ ሀገር መሆኗም መጻሕፍተ ታሪክን ባነበቡ ሊቃውንት አንደበት ብቻ ሳይሆን በማዳመጥ  ትውፊት /ርክክብ/ ለኅብረተሰቡ ኀቡእ ያልሆነ ነገር መሆኑ ነው ፡፡
በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ዑደት ስፍር ቀምር የራሷን  ዜማ ያደላደለች አፍሪካዊት እመቤት ናት ብንል ጽልመት ሊጋርደው የማይችለው ገሀድ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ እኛ ልጆቿ የትናንቱን ለዛሬ ትውልድ ማበርከት ያልቻልን ይመስላል ፡፡   ለዚህም ነው ትናንት የተነሱ የዜማ ሊቃውንት እነ ሞዛርት ከቅዱስ ያሬድ 1250 ዓመት ብኋላ የተወለዱት በዓለም የዜማ ሊቃውንት ሲባሉ ቀደምት የሆነው ቅዱስ ያሬድ ግን ኢትዮጵያውያን እንኳን ስራውን እንዳንዘክረው ስራዎቹን ተራ ስራ ተደርገው እንዲታዩ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም፡፡
አበው ለብዙ ዘመናት ይህን ዜማ  በዜማ ቤቱ፣ በቅኔ ቤቱ በመጻሕፍት ቤቱ እንዳልተጠቀሙበት ሁሉ ዛሬ ግን የአበው ያለህ ብለን  ቅዳሴውን በንባብና በአማረኛ ለውጠን ዜማው እነዲዘነጋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረግን ነው፡፡ ይህ ግን “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ሳያሠኝ አይቀርም ፡፡ 

ቢቻል ቀደምት የዜማ ምልክት ደራሲ መሆኑንም ጭምር ቤተ ክርስቲያን ለአለም የምታሳውቅበት ጊዜ ቢኖር ይህ ይመስለኛል ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ደግሞ እያንዳንዳችን ከዛሬ ጀምረን በየአጥቢያችን ታላላቅ በአላትን ተንተርሰን የሚዘከርበትን ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል ከመስቀል በዓል አከባበር ቢጀምር ባዮች ነን፡፡ በረከቱ ሁሌም አይለየን፡፡
ስራ ምግባር ባይኖረን የቅዱሳንን መንፈሳዊ ተጋድሎ ማውሳት መዘከርም ታላቅ ስጦታ ነው :: መንፈሳዊ ተጋድሎ የክርስቲያኖች ህይወት ለታላቅ ክብር የሚያበቃ በመሆኑ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበትን እና ለእግዚአብሔር የምንገዛበትን መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው፡፡ይኸውም ስለ ቅዱሳንን አባቶቻችን ተጋድሎ ማውሳት ለመንፈሳዊነታችን ታላቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በየዕለቱ የምንሰማው የቅዱሳን ሕይወትና ታሪክ እነርሱ ወደ ተጋደሉበት የቅድስና መንገድ የሚመራንና ለተሻለ የመንፈሳዊ ህይወት የምንገጓዝበት ትልቅ ድልድይ ነው፡፡ ያዕ 9፣7 .መዝ 72፣28
‘’ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል ‘’ 2ኛ ቆሮ 11፣14 ቅዱሳን ሁሉ ይህን የሰይጣን ተንኮል ፍጹም በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የራሳቸው አገልጋይ እስከማድረግ ደረጃ ደርሰዋል፣መሬት ተከፍታ እንድትውጠውም አድርገዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ጸጋ ሰጪ ባለቤቱ መድኃን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ስለዚህም ቅዱሳንን መሳደብ የክብር ጌታን መሳደብ ነውና አውሬው ራዕ 13፣6 ከዚህ ምግባሩ ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡ ’በዓለም ግን መከራ ትቀበላላችሁ ነገር ግን ጽኑ እኔ ዓለምን ድል ነስቼዋለሁ ‘’ዮሐ 16፣33  ለነቢያት፣ ለሐዋሪያት፣ ለአበው ቅዱሳን እና ለቅዱሳን እናቶቻችን የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ለማግኘትና ዲያብሎስን ድል ለማድረግ በጾም ፣በጸሎት ፈቃደ እግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ በመፈጸም መልካሙን የእምነት ገድል ፈጽመን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መሰረት አድርገን ሃይማኖታችንን እስከ ሞት ድረስ ታምነን እንድንጠብቅ የቅዱሳን አምላክ ይርዳን::
ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ቅዱስ ያሬድ በተወለደ በሰባት ዓመቱ አባቱ ስለሞተ እናቱ ክርስቲና የአክሱም ገበዝ ለነበረው ለአጐቱ ለጌዴዎን እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው ሰጠችው፡፡ ትምህርት አልዋሃድ ስላለውና ቁጣውና አለንጋው ስለበዛበት ጠፍቶ ማይኪራህ ወደምትባል ቦታ በመሰደድ በአንዲት ዛፍ ሥር አርፎ እያለቀሰ ሳለ አንድ ትል አየ፡፡ ትሉም 6 ጊዜያት በዛፉ ላይ እወጣለሁ እያለ ሲወድቅ፤ በሰባተኛው ግን ከዛፉ ላይ ወጥቶ የዛፉን ፍሬ ሲበላ አየ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ተስፋ አለመቁረጥን እግዚአብሔር ካዘጋጀለት ትል ተምሮና ወደ ልቡ ተመልሶ ወደ አጎቱ መጥቶ ይቅርታ በመጠየቅ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ብልህ ሰው በጥቂት ነገር ይማራል፡፡ እግዚአብሔርም ገለለትና በሚገባ ተማረ፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱስ ያሬድ መመስገንን በወደደ ጊዜም ከኤዶም ገነት ሦስት አእዋፋትን በመላክ እግዚአብሔር ወደ ሰማይ ጠራው፡፡ እርሱም ወደ ሰማይ ተነጥቆ 24 ካህናተ ሰማይ ሲያመሰግኑ ሰምቶ አይቶ ተመለሰ፡፡ ወዲያውም ከጧቱ 3 ሰዓትአክሱም ቤተክርስቲያን በታቦተ  ፅዮን ፊት ቆሞ «ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ» ብሎ በልሣነ ግእዝ ዘመረ የዜማውም ስልት አራራይ ነበር፡፡ ትርጓሜውም «ለአብ ምሥጋና ይገባል፣ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል ዮን አስቀድሞ እግዚአብሔር ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም ለሙሴ የድንኳኑን ሥራ አሳየ» ማለት ነው፡፡ ይህችን ዜማ ቅዱስ ያሬድ «አርያም» አላት፤ ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘች ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የተለያዩ ዜማዎችን ደርሷል፡፡
የቅዱስ ያሬድ የስሙም ትርጓሜ ብዙ ነው፡፡ ያሬድ ማለት «ራዕየ ምሥጢር፣ ነፃሬ ኅቡአት» ማለት ነው፤ የመላእክት ምስጢር የነበረውን  ጸዋተወ ዜማ አምልቶና አስፍቶ በመናገሩ፡፡ አንድም ያሬድ ማለት «ንብ» ማለት ነው፤ ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ ሁሉ ያሬድም ከመጻሕፍት የማይጠቅሰው የለምና፡፡ በንቡ የተቀሰመው ማር እጅግ ጣፋከመሆኑም በላይ ሰሙ ለመብራት ውሎ ጨለማን አርቆ ብርሃንን እንደሚሰጥ ሁሉ፤ የቅዱስ ያሬድም ዜማ ንባቡ ከምሥጢሩ ጋር ተዋሕዶ ምእመናንን ደስ ከማሰኘቱም በላይ መናፍቃንን የሚያሳፍር ለምእመናን ተድላ ደስታን የሚያበስር ኃይለ ቃሉ እንደ መብረቅ የሚያንባርቅ ጨለማ ክህደትን የሚያርቅ ብርሃነ ጥበብ የተመላበት ነው፡፡
ይቆየን…….ይቀጥላል ከአንድ ቀን ብኋላ ቀጣዩን ክፍል እናቀርባለን::
የቅዱስ ያሬድ በረከት ረድኤት አይለየን፡፡ አሜን::

1 comment:

  1. Thanks to Almighty God for all things he made,make and will make

    ReplyDelete