Friday, July 20, 2012

የ20 ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት


ሰማዕቱ  አቡነ  ጴጥሮ
« እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡  አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 .በሰማዕትነት አለፉ፡፡


1875 .. የተወለዱት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ  1921 .. በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ጊዜ ስትሾም አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ የመጀመርያ ጳጳሳት መካከል አንዱ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ፣ "ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ" ተብለው  21 አካባቢዎችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ 

የኢጣሊያ
ፋሺስት 1928 .. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ስፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ  እና በደቡባዊ ምሥራቅ  አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነው ጢሞቴዎስን የተሰጠውን አደራ በመጠበቅ ሓላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት እንደ ሚገባው ሲገልጽ «እቀብ ማህጸንተከ፤ አደራህን ጠብቅ» በማለት ነው፡፡ 1ኛጢሞ.6 .2፡፡ ጢሞቴዎስ በመምህሩ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የዚህ ዓለም ፈቃድ ሳያሸንፈው ተወጥቷል፡፡ የዓላውያን ነገሥታት ማዋከብ፣ ድብደባ አደራውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነትም ጉዞ መነሻውም መድረሻውም የእነዚህ አባቶች አርአያ ፍኖት ነው፡፡

ለሀገራቸውና
ለወገናቸው እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለሕዝባቸው የሰጡት ምስክርነት የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት ነው፡፡ አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን ብፁዕነታቸውን ጠርተው የሚከተለውን የአደራ ቃል ያስተላልፋሉ፡፡ «ኀይለማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፡፡ አደራ፡፡» /መርሻ አለኸኝ /ዲያቆን/ 1986 .ም፣ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ ገጽ.80/

ሐዋርያው
ቅዱስ ጢሞቴዎስ የመምህሩን የአደራ ቃል በመያዝ እስከ መጨረሻው እንደጸናው ብፁዕነታቸውም የመምህራቸውን የአደራ ቃል በሰማዕትነት አትመው ጠበቁ፡፡ አንዲትም ቀንና ሰዓት ከሞት ሳይሸሹ እና ሳይደበቁ ለአገራቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ ሞትን ተጋፈጡ፡፡ የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ የዚህ ምንጩ አደራ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በአደራ የሰጠቻቸውን ሓላፊነት ለመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በጸሎታቸው እየደገፉ፣ በትምህርታቸው እያበረቱ አስተዳድረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ችሎቱ ተሰይሞ ሲቀርቡ ዳኛው «ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለሥልጣናት ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ) ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት «አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» በማለት ሕያው በሆነ ቃላቸው መለሱ፡፡ ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡  አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው በሰማዕትነት አለፉ፡፡ / መርሻ አለኸኝ/ዲያቆን/ 1996.ም፣ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ገጽ.77/


ይህን መሰሉ ታላቅ የሰማዕትነት ገድል የዛሬዎቹ ጳጳሳትሰ  የትናቸው ያሰኛል እንደ አቡነ ጴጥሮስ ኃላፊነታቸውን እና አደራን የሚወጡ ናቸውን? ወይስ ከቤተ ክርስቲያን ልዕልና እና መታፈር ይልቅ ራሳቸውን በአገረ ስብከቶቻቸው ልዑላን በማድረግ የሾሙ ፤የአክሊለ ሦክ ምሳሌ የሆነውን ቆብ ማድረጋቸውን ዘንግተው ዘውድ የደፉ ይመስል በዙርያቸው «እራትአግባዎችን» አደራጅተው ለቤተክርስቲያን  የማኅፀን እሾኽ የሆኑ፤ የትኛውም አካል እነርሱን እስካልነካ ድረስ ቤተክርስቲያን ላይ «ቤንዚል አርከፍክፎ ፣ ክብሪት ጭሮ እሳት ቢለቅ» አባታዊ መዓዛ የማይታይባቸው፤  ኃላፊነትን ለመሸከም  እጅጉን የራቃቸው ሥጋውያን ናቸው:: በየገዳማቱ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ የገዳማቱን እና የየአድባራቱን መሠረታዊ ችግር ከሚፈታ ይልቅ እነርሱ ኪስ ሲገባ የሚያስደስታቸው፤ በየሀገረ ስብከቶቻቸው ያሉ ሊቃውንት በችጋር ሲሰደዱ፣ ወንበር ሲያጥፉ እነርሱ ግን መደለያ ያቀረቡላቸውን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ሲከባከቡ፣ ሽርጉድ ሲያበዙላቸው ይታያል፡፡ ከቤተክርስቲያኗ የአስተዳደር ሕግ እና ሥርዐት ውጭ በየሀገረ ስብከቶቻቸው የእኅት እና የአክስት ልጆቻቸውን የሚቆጥሩ፡፡ እነርሱም በአቅማቸው ቤተሰባዊ አስተዳደርን ያሳፈኑ ናቸው፡፡ ለምን) «ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ» ነውና፡፡ ከዚህ እውነታ ተነሥተን እነርሱ በፓትርያሪኩ ላይ ያነሡትን የቤተሰብ አስተዳደራዊ በደልን ስንፈትሽ ሞራላዊ ብቃት እንደሌላቸው ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ እነርሱም ቤተሰባዊ አስተዳደር ደዌ የተጣባቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው፡- እኛ እያለን አጽራረ ቤተክርስቲያን አይነኩም ባዮች የሆኑት፡፡ እነርሱ ለቤተክርስቲያን መከራ ከሚቀበሉ ቤተክርስቲያን መከራ መቀበሏን የፈቀዱት፡፡ እነርሱ ሞት ከሚቀምሱ ሥርዓቷን፣ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን ለሞት የዳረጉት፡፡ በአንድ ጀንበር የበር መሰበር ብትንትናቸው ወጥቶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍያው ቡድን ያስረከቡት፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ እና ሰማያዊ ሥልጣን መከበር ይልቅ የአባ እገሌ መሻር እና የአባ እገሌ መሾም ጉዳይ ሆኖባቸው በፍቅረ ሢመት /በሥልጣን ጥም/ አብደው በቤተክህነቱም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማየት የሚገባንን የአስተዳደር ለውጥ እንዳናይ ግርዶሽ ሆኑብን፡፡የጴጥሮስን ሥልጣን የያዙ፣ አስኬማውን የደፉ፣ ካባውን የደረቡ፣ መስቀሉን ከእነ በትረ ሙሴው የጨበጡት «ዘመነኞቹ» ጳጳሳት ከቤተክርስቲያን የተቀበሉትን የእረኝነት የአደራ ቃል በመተው ለቤተክርስቲያን ከሚታገሉላት ይልቅ የሚታገሏት ሆነዋል፡፡ ጵጵስናውን ሲቀበሉ የገቡትን ቃለ አደራ በመዘንጋት በጴጥሮሳዊነት ለአገርና ለወገን ሊቆሙ ይቅርና ክብርን ለአጎናጸፈቻቸው እናት ቤተክርስቲያን የማይሆኑ እርባና ቢስ ሆነዋል፡፡ ፍርሃት ድሩን ሠርቶባቸው ትምእርተ ምንኩስናቸውን ሸፍኖታል፡፡ ሹመታቸው የዖዝያን ሹመት እስኪመስል ድረስ የጽድቅ ፈሪዎች፤ የኃጢአት ደፋሮች አስመስሏቸዋል፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ፋሺስት ጣሊያን የእርሱ አቋም የራሳቸው አቋም፤ የእርሱ የጭቆና አገዛዝ የእርሳቸው አገዛዝ፣ የእርሱ ተራ ፕሮፓጋንዳ የእርሳቸው እውነት አድርገው እንዲቀበሉ መደለያ /ገንዘብ፣ መኪና በዘመኑ ዘመናዊ የሚባል ቤት/ ልስጦት ሳይላቸው ቀርቶ ነውን) ለሕዝባቸው፣ ለሀገራቸውና ለቤተክርስቲያናቸው ሰማዕት የሆኑት) እርሳቸው ግን መንኖ ጥሪትን ገንዘብ ያደረጉ አባት በመሆናቸው ሌሎቹ የቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ለፋሺስት ጣሊያን ሲያድሩ መደለያው ሳያንበረክካቸው በመንፈሳዊ ወኔ ሰማዕት ሆነዋል፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1982 .. ሰማዕቱን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ፣ ቀብራቸው በምስጢር መፈጸሙ መዛግብት እንደሚያስረዱ እና የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምስጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምስጢር ቀበሯቸውከሚል ጠቅላላ ፍንጭ ያለፈ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቆይቶ ነበር ፡፡

ከቅርብ
ዓመታት ወዲህ ግን ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞለቡተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረውሙኒሳ ጉብታላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ በእርግጠኝነት አስረድተዋቸዋል፡፡

በዚህም በፋሺስት ኢጣሊያ 76 ዓመት በፊት ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ የተቀበሩበት ቦታ በአዲስ አበባ በስተደቡብ በለቡ አካባቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አረጋግጣለች፡፡
« እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡  አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 .በሰማዕትነት አለፉ፡፡


ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ከጻፉት "ጴጥሮስ ያችን ሰዓት" ከተሰኘች ተውኔት አንዷን ቃለ ተውኔት "ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት" የግጥም እውነታም ሃይማኖታዊ ትውፊትን ይጠቅሳል፡፡ የትውፊቱ ጭብጥ እመ ብርሃን ኢትዮጵያን ትጠብቅና ስለ ኢትዮጵያ ታማልድ ዘንድ፣ ኢትዮጵያ ከልጅዋ ከኢየሱስ የተሰጠቻት የአስራት አገሯ ናት የሚል ነው፡፡
“አዬ፣ ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀንዋን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ
እኮ ማንም የላት?"


ታላቅ አባት፣ ታላቅመሪ፣ አኩሪ ገድል፣ የቤተክርስቲያን አለኝታ የዘመናችን ታላቅ ሰማዕት፡፡ ያልተዘመረላቸው፣ ያልተነገረላቸው ፣ያልተሰበከላቸው፣ ዛሬ ይህ ትውልድ ሊያስብላቸው የሚገባ ልዩ ኃብታችን ናቸው፡፡

ከሰማዕቱ በረከት ረድኤት ምልጃ አምላክ ያሳትፈን::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ::  

2 comments:

  1. “አዬ፣ ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
    ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
    እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
    ልቦናሽን ታዞሪባት?
    ፈተናዋን፣ ሰቀቀንዋን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
    አላንቺ እኮ ማንም የላት?"

    ReplyDelete
  2. « እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በሰማዕትነት አለፉ፡፡

    ReplyDelete