Wednesday, August 31, 2011

«የአሮጊቷ ሣራ» ወለደች ዐዋጅ ተሐድሶ ዘመቻ የጥፋት ፈትል እንደማጠንጠኛ

http://www.facebook.com/video/video.php?v=126800684079140&saved

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በብሉያትና በሐዲሳቱም የምትነሣው ሣራ አበ ብዙኃን ሥርወ ሃይማኖት የምንለው የአብርሃም ሚስት ነች፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የብዙዎች አባት እንዲሆን ቃል ኪዳን ሳይገባለት በፊት፣ በመካንነት ታዝን፣ ተስፋም አጥታ ትተክዝ በነበረችበት ጊዜ ሦራ ትባል ነበር፡፡

ሦራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ ልጅ እንደምትወልድ ከአብርሃም በኩል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከገባላት፣ ተስፋም ከተሰጣት በኋላ ሣራ ተብላለች፡፡ እግዚአብሔርም ስለእርሷ ለአብርሃም «የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፤ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ፤ እባርካታለሁ፤ ደግሞም ከእርሷ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፤ የአሕዛብ እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ» በማለት ተናገረው /ዘፍ. 17፥15/፡፡

ሣራ ሦራ ተብላ ትጠራ በነበረበት፣ ያለተስፋ በኖረችበት የቀደመው ዘመኗ ለአብርሃም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፡፡ ሦራ ዘር ማጣት ታላቅ ሐዘን በሆነበት በዚያ ዘመን፣ መካንነት ያስንቅ በነበረበት በዚያን ጊዜ አብራም ከሌላ ይወልድ ዘንድ አዘነችለት፡፡ አብራም አጋር ወደ ተባለችው ግብጻዊት ባሪያዋ ይደርስ ዘንድ «እነሆ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ ምናልባት ከእርሷ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርሷ ግባ» አለችው፡፡ /ዘፍ.16፥2/ በትሑቷ ሦራ ምክር አጋር ከአብርሃም በፀነሰችበት ወራት ሦራን አሳዘነቻት፤ አጋርም ተመካች፤ እመቤት የነበረችውን ሦራ ስለመካንነቷ በዓይኗ አቃለለቻት፡፡ ይህ ለሦራ በእግዚአብሔር እና በባሏ በአብራም ፊት ያዘነችበት ሰቆቃዋ ነው፡፡ ሦራም ከሐዘኗ ጽናት የተነሣ አብራምን እንዲህ አለችው «መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይኗ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ» አለችው፡፡ በአብራም ፍርድም ሦራ ባሪያዋን አጋርን በመቅጣቷ አጋር ኮበለለች፡፡

እንግዲህ ከላይ አስቀድመን የጠቀስነው ለአብርሃም የተገባው ቃል ኪዳን የተሰጠው ሦራና አብራም በዚህ ሐዘን ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያዘነችው ሦራ ከቃል ኪዳኑ በኋላ የብዙኃን እናት ልትሆን ሣራ ተብላ እርሱም የብዙዎች አባት ሊሆን አብርሃም ተብሎ የተስፋው ቃል ተነገረው «በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃልኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ» /ዘፍ.17፥19/፡፡

እግዚአብሔር ለአብርሃም ሣራ እንደምትወልድ የነገርውን የተስፋ ቃል በቤቱ በእንግድነት ተገኝቶ አጸና፡፡ «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች፡፡»/ዘፍ.18፥10/ አለው፡፡ ሁል ጊዜም ቃሉ የሚታመን እግዚአብሔር ይመስገንና እንደተባለው ሆነ «እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሣራን አሰበ እግዚአብሔርም እንደተናገረው ለሣራ አደረገላት ሣራም ፀነሰች እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት አብርሃም ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው» /ዘፍ.21፥1/ «ሣራም እግዚአብሔር ሳቅ /ደስታ አድርጎልኛል ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች ደግሞም ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና /ዘፍ. 21፥7/፡፡

እንግዲህ መካኒቱ ሣራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ በጨዋነት ወልዳ ለአብርሃም ለዘላለም የገባው ቃል ኪዳን የሚፈጸምበትን ዘር ይስሐቅን አሳድጋለች፡፡ በቃል ኪዳን፣ በተስፋ የተወለደው ይስሐቅ ታላቅ ነውና «የዚህች ባሪያ /የአጋር/ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስም» አለች፡፡ እግዚአብሔርም ቃሏን ተቀብሎ ለአብርሃም «ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና...» አለው /ዘፍ.21፥1-12/፡፡

እንዲህ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የከበረችው ሣራ በብሉያት ብቻ ሳይሆን በሐዲሳትም ለተለያዩ ጉዳዮች እንደ አርአያና ምሳሌ ስትጠቀስ እናነባለን፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቶችን ሲመክር በመልካም ትሑት ሰብእናዋ አርአያ የምትሆን አድርጎ የጠቀሳት ሣራን ነው «ጠጉርን በመሸረብ፣ ወርቅን በማንጠልጠል፣ ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጪ በሆነ ሽልማት» ሳይሆን «በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ» ተጎናጽፋ ውስጧን ያስጌጠች ብፅዕት ሚስት መሆኗን መስክሯል፡፡ «ሣራ ለአብርሃም ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ፡፡» /1ጴጥ. 3፥3-6/ ብሏል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የክርስቶስ የማዳኑ የምስራች ከታወጀላቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ካልጠበቅን አንድንም የሚሉ ቢጽሐሳውያንን ቃል ሰምተው ያመኑ የገላትያን ሰዎች በገሰጸበት መልእክቱ ሣራን የሕገ ወንጌል ምሳሌ አድርጎ አቅርቧታል፡፡ በአንጻሩ ባሪያዋን አጋርን የሕገ ኦሪት ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል /ገላ.4፥21/፡፡

የሣራን ሕይወት በዚህ ጽሑፍ ያነሣንበትንም መሠረታዊ ምክንያትም ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ምሳሌያዊ መልእክት ተንተርሰው ያለአገባቡ እየጠቀሱ የቤተ ክርስቲያናን ልጆች ምእመናንን ግራ ስለሚያጋቡ የተሐድሶ መናፍቃንና ተሐድሶአዊ ትምህርት ስለሚያስተምሩ ሰዎች ሐሳብ ለማንሣት ነው፡፡ በቅድሚያ የቅዱስ ጳውሎስ የመልእክቱን ሐሳብ በአጭሩ እናብራራና፤ ተሐድሶ የዘመቻ ማወራረጃ አድርጎ ስለሚጠቀምበት ጥራዝ ነጠቅ ቃልና አስተሳሰብ ደግሞ ቀጥሎ እናመጣለን፡፡ ሐዋርያው ስለዚህ ነገር ሲናገር የሚከተለውን ብሏል፡፡

«እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ? እስኪ ንገሩኝ፤ አንዱ ከባሪያዪቱ አንዱ       ከጨዋዪቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደነበሩት ተጽፏልና፤ ነገር ግን የባሪያዪቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዷል፤ የጨዋዪቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዷል፤ ይህም ነገር ምሳሌ ነው እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳናት ናቸውና፤ ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፤ እርሷም አጋር ናት፤ ይህቺም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጆቿ ጋር በባርነት ናትና፤ ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት፤ እርሷም እናታችን ናት... ስለዚህ ወንድሞች ሆይ የጨዋዪቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያዪቱ አይደለንም» /ገላ.4፥21-31/፡፡
በገላትያ መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ «የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች» ስለነበሩት ከአይሁድ ወገን የሆኑ ካልተገረዛችሁ፣ ሕገ ኦሪትንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ኦሪታዊ ሁኑ የሚሉ ሰዎችን ትምህርት እየሰሙ የወንጌልን ቃል ቸል ያሉት የገላትያን ሰዎች በግልጽ «እግዚአብሔርን ስታውቁ፣ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን ? ቀንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ...» ይላቸዋል፡፡ /ገላ.4፥9-11/
የሐዋርያው ዋነኛ ጉዳይ ሕገ ኦሪት ይጠበቅ አይጠበቅ በመሆኑም ነው «እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ?» ያላቸው /ገላ. 1፥21/፡፡ ምክንያቱም ያመኑትን ሁሉ በደሙ የዋጀ የኢየሱስ ክርስቶስ የምስራች ወንጌል ከተነገረች በኋላ ዳግመኛ ወደ ኋላ ተመልሶ ቀንና ወርን ዘመንንም እየቆጠሩ መሥዋዕተ ኦሪትን ለማቅረብ፣ ግዝረትን አበክሮ ለመጠበቅ፣ ያንንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም ወደሚል ትምህርት መመለስ ያሳፍራልና፡፡
ስለዚህ እናንተ በኦሪት እንኑር የምትሉ ሆይ! በኦሪት የተነገረውን ምሳሌ አንብቡ ብሎ የሣራን እና የአጋርን ምሳሌነት ያነሣል፡፡ በኦሪት አብርሃም አስቀድመን እንዳየነው ጨዋይቱ ከተባለችው ከእመቤቲቱ ሣራ ይስሐቅን፣ ከባሪያይቱ ከአጋር ደግሞ እስማኤልን ወልዷል፡፡ የሁለቱ ልደት ግን ለየቅል መሆኑን ይነግራቸዋል፡፡ ከባሪያዪቱ የተወለደው አጋር ሙቀት ልምላሜ እያላት ተወልዷልና፤ ከእመቤቲቱ የተወለደው ግን ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በዘጠና ዓመቷ/ ከእግዚአብሔር ብቻ በተሰጠው ተስፋ ተአምራትም ተወልዷልና፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሴቶች የሕገ ኦሪትና የሕገ ወንጌል ምሳሌ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቃሉ «ይህም ነገር ምሳሌ ነው» እንዳለ /ገላ. 4፥24/፡፡ አጋር ኦሪትን ደብረ ሲናን አንድ ወገን ያደርጋል፤ ሣራን፣ ወንጌልን ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌምን ደግሞ አንድ ወገን እያደረገ እያነጻጸረ ተናግሯል፡፡
አንዲቱ /ኦሪት/ አምሳል መርገፍ ሆና በደብረ ሲና ተሠርታለችና፤ ደብረ ሲናም ከኢየሩሳሌም ስትነጻጸር በምዕራብ ያለች ተራራ ናትና፤ ስለዚህ ይህች ምድራዊት የምትሆን አምሳል መርገፍ አማናዊት ከምትሆን ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ጋር ስትነጻጸር ዝቅ ያለች ናትና «ወትትቀነይ ምስለ ደቂቃ» አምሳል መርገፍ በመሆን ከልጆቿ ጋር ትገዛለች፡፡ ላዕላዊት የምትሆን ኢየሩሳሌም ግን ከመገዛት ነጻ ናት ብሎ «ወይእቲ እምነ፤ እርስዋም እናታችን ናት» ይላል፡፡ ይቺም እናታችን ሣራ ምሳሌዋ የምትሆን ወንጌል ናት፡፡
ስለዚህ ከሣራ የተወለደው ተስፋውን ወራሽ እንደሆነ ሁሉ እኛም ከወንጌል የተወለድን ክርስቶሳውያን በይስሐቅ አምሳል እንደይስሐቅ ተስፋውን መውረስ የሚገባን የነጻነት ልጆች ነን ማለቱ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስተምራሉ፡፡ የባሪያዪቱ ልጅ ከእመቤት ልጅ ጋር ተካክሎ ርስት አይወርስምና በበግና በፍየሎች ደም ምሳሌያዊ ወይም ጥላ   አገልግሎት በምትሰጥ ገረድ /ሞግዚት/ የተባለች የኦሪት ልጆች አይደለንም፡፡ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ልጅ ሥጋና ደም ነጻ በምታወጣ አዲስ ኪዳን የወንጌል ልጆች ነንና፡፡
ሐዋርያው ይህንን ሁሉ ያለው ካልተገረዛችሁ አትድኑም የሚለውን የቢጽ ሐሳውያንን ትምህርት በመኮነን ሲሆን ይህንንም በግልጽ «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና /ገላ. 5፥6/ ይላል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ ያለው ሕይወትም ፍትወተ ሥጋን አሸንፎ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የበቁ ሆኖ በመንፈስ መራመድን ነው፡፡ ይህ ሣራ በተመሰለችባት ሕገ ወንገል ውስጥ የተጠራንበት የመታዘዝ ሕይወት ነው፡፡ ሐዋርያውም ለገላትያ ሰዎች ይህንኑ ተርጉሞ ሲናገር «የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ» /ገላ. 5፥24/ አለን፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞት ጋር የሰቀሉ መንፈሳውያን፣ በፍቅር የእግዚብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽመው የጨዋይቱ /የእመቤቲቱ/ የሣራ ልጆች ናቸው፤ እንጂ ሥጋዊ ሥርዓት፣ መርገፍ፣ ጥላ በሆነው ብሉይ ኪዳን ውስጥ የመገረዝ አለመገረዝ ጣጣን የሚሰብኩ፣ የሚሰበኩ በሥጋ ልማድ የወለደችው የባሪያዪቱ የአጋር ልጆች አይደሉም፡፡
እንግዲህ በነጻነት የምትመራውን ላይኛይቱን ኢየሩሳሌምን የመረጡ ክርስቶሳውያን ለ2ሺሕ ዘመናት ያህል ክርስቶስን በመስበክ በስሙም ክርስቲያን ተብለን ስንጠራ ኖረናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ገና አስቀድሞ በ34 ዓ.ም «ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ካለው ጃንደረባው ጀምረው ሠልጥና ከነበረችው ባሪያይቱ አጋር ይልቅ በተስፋው ሥርዓት የወለደችውን እመቤቲቱን ሣራ መርጠው እስከዚህ ዘመን ድረስ ኖረዋል፡፡
ከየካቲት ወር 1990 ዓ.ም ጀምሮ ግን «ተሐድሶ» በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በይፋ በጀመረው ዘመቻ ውስጥ የዘመቻው አዋጅ ማጠንጠኛ «አሮጊቷ ሣራ እኔ /እኛን/ ወለደች» የሚለው ቃል ነው፡፡ «የተሐድሶ መነኮሳት ኅብረት» የተባለው ቡድን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሆኖ ከቤተ ክርስቲያን ማዕድ እየተቋደሰ ነገር ግን በመሠሪነት ለመናፍቃን ተላላኪ ሆኖ የቆየ ሲሆን በየካቲት ወር 1990 ግን በአዲስ አበባ ከተማ በኢግዚብሽን ማዕከል በፕሮቴስታንቶች ተደራጅቶ በተዘጋጀው «ጉባኤ» በይፋ ራሱን ለይቶ የ«ተሐድሶ» ጥሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲደረግ ሲያውጅ ተገኝቷል፡፡ /ይህንን ለማጋለጥ የወጣወን ቪዲዮ ፊልም ወይም ቪሲዲ ይመልከቱ/ በዚህ አዋጅ በጉልህ የሚስማው ድምፅ ከላይ የተጠቀሰው «አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች» የሚለው ንግግር ነበር፡፡ ይህንን ቃል ደጋግሞ ሲያስተጋባ የነበረው አባ ዮናስ /በለጠ/ የተባለው «መነኩሴ» «ወንጌልን ለመስበክ ተሾምኩ፤... አሮጊቷ ሣራ ወለደች፤ አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች፣ ዘውዱን ወለደች፣ ፍስሐን ወለደች፣ ገብረ ክርስቶስን ወለደች... ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል...» ወዘተ እያለ አብረውት ለጥፋት የተሰለፉ ከሃዲ መነኮሳትን እየጠቀሰ ፎክሯል፡፡
በእነ አባ ዮናስ አዋጅ ውስጥ ያለው ግልጽ መልእክት ግን በሁለት መልኩ የሚታይ ወይም ሊተረጎም የሚችል ነው፡፡
1.    ቤተክርስቲያንን በእርጅና ዘመኗ ከወለደችው ከቅድስት ሣራ ጋር በማነጻጸር ራሳቸውን የዚህችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አድርገው በማቅረብ ከዚህች ቤተክርስቲያንም አካል የተገኙ መሆናቸውን በመግለጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እነርሱ የሚሉት እንደሆነ አድርገው ለማደናበር ነው፡፡
2.    ሌላው የድፍረት መልእክት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በባሪያይቱ በአጋር ምሳሌ ልትጠቀስ የምትችል ኦሪታዊት፤ የጨዋይቱ የተባለች የሣራ የተስፋው ዘር ቅሪት የሌለባት፣ የወንጌል ብርሃን ያልበራባት፤ ክርስቶስን የማታውቅ፣ ጌትነቱንም የማታምን አድርገው አቅርበዋታል፡፡ ራሳቸውንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወንጌልን ለማድረስ የተሾሙ በኩራት አድርገው አቅርበዋል፡፡
የመጀመሪያውን ትርጉም ወይም መልእክት በማጉላትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም የዚህን የ«ተሐድሶ» መሠሪ አካሔድ በውል በመረዳት አውግዞ በመለየትና ውግዘት በማስተላለፍ ለ2ሺሕ ዘመናት ወንጌልን ስትሰብክ የነበረች ቤተ ክርስቲያንን ልዕልናና ክብር አጉድፎ በወንጌል ሰባኪነት ስም በማጭበርበር ፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ለመዝራት ተሐድሶ እያደባ መሆኑን አጋልጧል፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነት ከሰጠው ሰፊ መግለጫ ውስጥ ይህን የተመለከተውን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡

«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» የሚል ኃይለ ቃል መናገራቸው ተዘግቧል፤ መናፍቃኑ ይህን የተናገሩት የእነሱን ከጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን አፈንግጦ መውጣት የዘጠና ዓመት እድሜ ከነበራት እና ከቅድስት ሣራ ከተወለደው ከይስሐቅ ልደት ጋር ለማነጻጸር በመፈለግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የይስሐቅ እናት ቅድስት ሣራ በመሠረቱ እናትና አባቱን የሚያከብርና የሚያስከብር እንጂ የሚያዋርድ፣ እናትና አባቱን የሚያስመሰግን እንጂ ሰድቦ የሚያሰድብ፣ በእናትና አባቱ እግር የሚተካ እንጂ እናትና አባቱን የሚክድ፣ በወላጆቹ የተመረቀ እንጂ የተረገመ ልጅ እናት አይደለችም፡፡

በቅድስት ሣራ አምሳል የተጠቀሰችው ጥንታዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲሁ እናቱን ለመሸጥና ለመለወጥ የሚያስማማ፣ እናቱን ሲሰድብና ሲነቅፍ ሐፍረት የማይሰማው ርጉም ልጅ እናት አይደለችም፤ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለ ልጅ አልወለደችም፣ አትወልድምም፡፡

ጠላትና አረም ሳይዘሩት ይበቅላል እንደሚባለው፣ በአንድ የስንዴ ማሳ ላይ የበቀለ አረም ቢኖር ያ አረም ሳይዘራ የበቀለ መሆኑን ማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደማይሆን ሁሉ እነዚህ መናፍቃንም በቤተ ክርስቲያናችን የስንዴ ማሳ ላይ ሳይዘሩ የበቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በምሳሌ ዘር እንደተጠቀሰው /ማቴ.13፥24-30/ በንጹሕ ስንዴ ማሳ ላይ ጠላት የዘራው ክርዳድ ሊበቅል እንደሚችልም ታውቋል፡፡ እነዚህ መናፍቃንም የጠላት እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን አበው ተክል ባለመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተወለዱ አድርገው ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ የማን ልጆች እንደሆኑ ቢጠይቁ ዕውነቱን ለማወቅ በቻሉ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ «በኋላ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ገንዘብን የሚወድዱ፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ሐሜተኞች፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ የማይወዱ ከዳተኞች ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ይክዱታል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን፣ ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉትን... የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና» /1ጢሞ. 3.1-7/ ሲል እንደተናገረው እነዚህ መናፍቃን ከዚህ የትንቢት ዘመን የተወለዱ እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች አለመሆናቸውን በግልጽ መንገር ግዴታ ይሆናል፡፡ /መጋቢት 26 ቀን 1990 ዓ.ም/
ጠቅላይ ቤተክህነት የተነተነበት መንገድ እንዳለ ሆኖ የ«ተሐድሶ» ቡድን «አሮጊቷ» የሚለውን ቃል የመረጠበትን መሠረታዊ ምክንያት በውል ማጤን ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የምትሰብክን ቤተ ክርስቲያን ከቅድስት ሣራ ጋር አነጻጽሮ ባቀረበበት መንገድ አስበው ተናግረውት ቢሆንማ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አፈንግጠው የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ባዘጋጁት በዚያ የስድብ ጉባኤ ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት ትምህርትና ሥርዓት የምእመ ናንን ሕይወት ባላዋረዱ ባላናናቁ ነበር፡፡ ነገር ግን «አሮጊት /አሮጌ» የሚለውን ቃል የመረጡት ቤተ ክርስቲያን አርጅታለችና ማደስ አለብን ለሚለው አስተሳሰብ መንደርደሪያ ነው፡፡ እነዚህ የተሐድሶ መናፍቃን ተወግዘው ቢለዩም በውጪም በውስጥም ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ለመገዝገዝና አስተምህሮአቸውን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ «መምህራን» አውቀውም ሳያውቁም በየዓውደ ምህረቱ እንዲያስተጋቡ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡

እነ አባ ዮናስ የ«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» ቃላቸውን ከአዋጁ ከ12 ዓመታት በኋላ አሁን በይፋ ደግሞ «ቤተ ክርስቲያንን አሪታዊት፣ ጨለማ ውስጥ ናት ሲሉ አሮጊቷ ሣራ ዛሬ እኔን ወለደች፣ እገሌን ወለደች፣ እገሌን ወለደች...» የሚል ከእነ አባ ዮናስ ጋር የቃልና የስሜት ዝምድና ያለው የአዋጅ ቃል በአንዳንድ ሰባኪያን ነን ባዮች ተሰምቷል፡፡ በአባ ዮናስና በእነዚህ ሰባኪያን መካከል ያለው የአቀራረብ ልዩነት የአባ ዮናስ በኤግዚቢሽን ማዕከል፣ እነዚህ ደግሞ በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓውደ ምህረት ላይ ማወጃቸው ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው ትምህርት ቃሉም ትርጓሜውም የታወቀ ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያናችንም ከጨዋይቱ የተወለድን ክርስቲያኖች አንድነት መሆኗ ለ2ሺሕ ዘመን የተመሰከረ ሆኖ ሳለ የአሁኖቹ «ሰባክያን» ራሳቸውንና ጓደኞቻቸውን ነጥለው «የተስፋው ወራሾች የአሮጊቷ የሣራ ልጆች» እያሉ የሚያቀርቡበት ገለጻ ትርጓሜ ይፋ መሆን አለበት፡፡

በመሠረቱ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ የተሰበከውን ምሳሌያዊ ትምህርት ይዞ ተንትኖ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ባሉበት ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ራሳቸውንና እነርሱ የመረጧቸውን የቡድን አባላት አባ ዮናስ ባቀረቡበት መንገድ «የአሮጊቷ ሣራ» ብሎ የጠሩበት ቤተ ክርስቲያን እነርሱን ከመውለዷ በፊት ምን ጎድሎባት፣ ምንስ አጥታ ነበር ? ቅዱስ ጳውሎስ መካኒቱ፣ ጨዋይቱ፣ እመቤቲቱ እያለ የጠራበት ቅጽል እያለ «አሮጊቷ» የሚለውን በማስጮኽ ማቅረብስ ለምን ተፈለገ ? ቀጥተኛ ምንጩስ ማነው ? ምንድነው ? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡ እነ አባ ዮናስ «አሮጊቷ ሣራ» ያሏትን ቤተ ክርስቲያንን ድንግል ማርያምን፣ ተክለሃይማኖትን፣ ጊዮርጊስን በልብሽ አኑረሻልና አውጪ እያሉ በአደባባይ ድፍረት ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ «ሰባክያን» የ«አሮጊቱ ሣራ» አስተምህሮ ውስጥ ያለው አንድምታስ ምንድነው ? እነ አባ ዮናስ በ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮአቸው «ቤተክርስቲያኒቱ በ4ኛው ክፍለ ዘመን አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ከሰበኩበት ጊዜ በኋላ ወንጌል አልተሰበከችም የወላድ መካን ሆና የኖረች ናት» በማለት አሁን እነርሱ ያንን ለመፈጸም የተወለዱ አድርገው አቅርበዋል፡፡ የእነዚህ ሰባክያን የ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮስ ከዚህ አንጻር ምን ይላል ?

ይህ ብቻ ሳይሆን አባ ዮናስ «ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል» ያለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዒላማ ያደረገ ፉከራው በእነዚህ ሰባክያን የመዝሙር መንደርደሪያዎች ውስጥ ከሚነገረውና «መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት ኢያሪኮን ያፈርሳል...» ከሚሉት አዝማች ቃል ጋር ያለውንም የትርጉም ዝምድና መጤን እንዳለበት         እንድናስብ ያስገድዳል፡፡ በተመሳሳይ ይህንኑ መንገድ ተከትሎ በየደረጃው ምእመናን እነ አባ ዮናስ በግልጽ ያወጁት የ«ተሐድሶ» ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ዓውደ ምህረቶቻችን ላይ አሁንም ወደቆሙ «መምህራን» መሻገር አለመሻገሩን ቃሎቻቸውን እያጠኑ ለመመርመር ተገደዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የሚመለከታቸው አካላትም የእነዚህን «ሰባኪያን» ትምህርት መርምረው ካለማወቅ በስሕተት የቀረበ ትምህርት መሆኑን ወይም በድፍረት የቀረበ ለ«ተሐድሶ» ዘመቻ የጥፋት ፈትል ማጠንጠኛ መሆን አለመሆኑን ለይተው እንደሚያቀርቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ by



Tuesday, August 30, 2011

‹ቤተክርስትያኒቷ ትዘጋ›› የሚል ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ


‹‹የገሀነም ደጆች አይችሏትም››
ጊዜው ወርሀ ክረምት ነው :: የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፆመ ፍልሰታ ወቅት ሲሆን በቤተክርስትያናችን ህግና ስርዓት መሰረት ይህ ጊዜ ዲያቆናት ፤ ካህናት መነኮሳት ፤ ጳጳሳት እና ምእመናን ለሐዋርያት የተገለፅሽላቸው እናታችን ለእኛም በምህረት አትለይን እያሉ በፆም ፤ በፀሎት ፤ በስግደት የሚለምኑበት ጊዜ ነው፡፡

ቦታው በሐረር መንገድ አዋሽ ሰባትን አልፈው ካለው የጉምሩክ የፍተሻ ጣቢያ ትንሽ ኪሎ ሜትር አለፍ ብሎ ከአሰቦት ገዳም መገንጠያ ሳይደርስ ከዋናው አስፋልት አንድ ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ የአባታችን የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ሲሆን የቦታው ስም ቦርደዴ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ቤተክርስትያን የሚገኝበት ቦታ ላይ ከ30 የማይበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ሲገኙ በቁጥር ከ40 እና ከ50 እጥፍ ልቀው የሚገኙት ግን ሙስሊም ማህበረሰቦች ናቸው፡፡ ይህ ቦታ ለአንድ አፍታም ቢሆን ከነገር እና ከትንኮሳ እፎይ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ቦታ ድረስ ሄጄ በተመለከትኩበት ጊዜ እዚህ ቦታ ላይ ያለው የሙቀት መጠን ክረምት ሳይል በጋ ከ40 ድግሪ በላይ ስለሆነ ቆሞ ማስቀደስ እንደ እግዚሐብሔር መልካም ፍቃድ ፤ ምህረት ፤ ቸርነት እንጂ እንደ እኛ ብርታትና ጥንካሬ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፡፡

ቤተክርስትያኒቷ አካባቢ ያሉት ምዕመና ጧፍ ፤ እጣን ፤ ዘቢብ እና ንዋየ ቅዱሳትን ማሟላት አቅሙ ስለሌላቸው ይህ ችግር የቀን ተቀን የውስጥ ችግር ችግራቸው ሆኖ አሁንም አሉ ፡፡ የባሰ አታም ነውና  አንድ ጊዜ ቅዳሴ ላይ ወንጌል ለማንበብ ጧፍ አልቆ በኩራዝ የተጠቀሙበት ጊዜም ነበር ፡፡
በአካባቢው የሚገኙ ከአክራሪ ወገን የሚመደቡት የእስልምና ተከታዮች በአካባቢው ላይ ለ24 ሰዓት ያህል ከ4 በሚበልጡ መስኪዶቻቸውን ድምፅ ማውጫ Speaker ወደ ቤተክርስትያን አዙረው ‹‹አላህ ዋክበር›› በሚሉበት ሁኔታ ላይ ምንም ጥያቄ ያላቀረቡት በአካባቢው የሚገኙ  ክርስትያኖች በዓመት አንድ ጊዜ ለ16 ቀናት ብቻ ያለውን የሱባኤ ጊዜ ለሊት ሰዓታት እና ኪዳኑ ፤ ጠዋት ትርጓሜው እና ስብከቱ ፤ ከሰዓት ቅዳሴው ረበሸን ብለው ቤተክርስትያኒቷ እንድትዘጋላቸው  ለአካባቢያቸው ወረዳ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው መጠየቃቸውን አረጋግጠናል፡፡ ይህን ጥያቄ የመስተዳድሩ  ሃላፊ ከሰማ በኋላ ለሚቀጥለው ቀን የቀጠራቸው ሲሆን በሚቀጥለው ቀን ሲመጡ ምንም ምላሽ ስላላገኙ ሓላፊውን በኃይል ከቢሮ ያባረሩት ሲሆን ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው የክልሉ መንግስ ጋር እንደደረሰ ፤ አካባቢው ላይ የሚገኙ ክርስትያኖች ጉዳዩን ወደ ፊደራል መንግስት የወሰዱት ሲሆን መንግስት የዛኑ ቀን ማታ አካባቢው ላይ የሚገኙ ፌደራል ፖሊሶች ማታ 3፡00 አካባቢ ወደ አካባቢው በፓትሮል በመምጣት ይህን ጥያቄ የጠየቁትን ሰዎች ግማሽ ያህሉን ለቅመው ወስደው ወደ እስር ቤት የከተቷቸው  ሲሆን የተቀሩትን ግን ሸሽተው አምልጠዋል፡፡ መንግስት ይህን እርምጃ ከወሰደ በኋላ ሁኔታውን በጥቂቱ ያረጋጋ ሲሆን ፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው በፊደራል ፖሊስ  እየተጠበቀ ይገኛል::

እኛ በአሁኑ ሰዓት እንትና 18 ገፅ ወቀሳ ፃፈ ፤ ያኛው ሰባኪ አውደ ምህረት ላይ እንዳይቆም ተከለከለ ፤ በዚህ መፅሄት ላይ እንትና መልስ ሰጠ ፤ አንዱ ይቅርታ አለ ሌላኛው ይቅርታ ተቀበለ እያልን ስራ መስራት በሚገባን ወቅት ወሬ ስናራግብ ለቤተክርስትያን መሆን በሚገባን ሰዓት ጊዜያችንን እና አቅማችንን አልባሌ ቦታ ላይ በማዋልና ትርፍ የሌለው ስራ በመስት ላይ እንገኛለን፡፡

አሁንም ጊዜው አልረፈደም ስለ ጥቂት ሰዎች ማውራታችንን አቁመን ስለ ቅድስት ቤተክርስትያን ዘብ እንቁም ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ይህን የጠየቁ ሰዎች ነገ ምን ማድረግ እንደሚያስቡ ለማስረዳት መምህር ሊያሻን አይገባም፡፡

በዚች ምድር ላይ የምንቆየው እንደ ማቱሳላ 969 ዓመት አለመሆኑን አውቀን በኖርንበት፤በምንኖርበት  ጊዜ ሁሉ ከቤተክርስትያን ጎን ለመቆም ያብቃል፡፡
እግዚሐብሔር ቤተክርስትያንን ይጠብቅ  
by አንድ አድርገኝ

Friday, August 26, 2011

ድንግል ማርያምነኝ ባይዋ ሴት ክስ ሊመሰረትባት ነው

  ..ድንግል ማርያም.. ነኝ ባይዋሴት ክስ ሊመሰረትባት ነው
  • አንዲት የ19 ዓመት ወጣት ሞታለች
  • • እናቴ ከመቃብር በመላዕክት ታጅባ አርጋለች
  • • ሦስት ልጆቿን በመንፈስ ቅዱስ ወለድኳቸው ትላለች፤  ባሏም ተስማምቷል
  • • ህፃናትን ለሦስት ቀናት፤ አዋቂዎችን ለስምንት ቀናትስታፆም ነበር
  • .የሥላሴ መንፈስ በእኔ ላይ አድሯል፤ ከእግዚአብሔር የተላክሁ ማርያም ነኝ.. በሚል ድንኳን በመኖሪያ ቤቷ አካባቢ ተክላ ተከታዮች ስታፈራና እምነቷን ስታስፋፋ የነበረችው ሴት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተካሄደባት ነው፡፡
በአምቦ ከተማ ገላን በተባለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ተወልዳ በ1994 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ትዕግስት ብርሃኑ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ..ማርያም ነኝ.. በሚል ማሳሳቻ ተከታዮችን አፍርታ እንደ ነበር ከፖሊስ የተገኘ ማስረጃ ይጠቁማል፡፡
በዚሁ ዓመት የፋሲካ በዓል ሰሞን ..እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቼ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ.. በማለት ዝግጅት የጀመረችው ትዕግስት፤ የስቅለት ዕለት የእሾህ አክሊልና የምትሰቀልበትን መስቀል አዘጋጅታ ጀርባዋን እንደ ተገረፈች ታውቋል፡፡ በመስቀሉ ላይ መሰቀሏን ያየ ግን አልተገኘም፡፡ በሦስተኛው ቀን ትዕግስት ከሞት ተነሳች ተብሎ ለአካባቢው ህዝብ እንደታየች ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የት ደርሳ እንደመጣች የጠየቃት ስለመኖሩ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ አብረዋት ይኖሩ የነበሩት አባቷ አቶ ብርሃኑ ድርጊቷን አጥብቀው ይቃወሙ እንደነበር የሚናገሩ ምንጮች፤ ጠጥተው ቤት ሲገቡ በጉዳዩ ይነታረኩ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ አባቷ ግን የልጃቸውን መለኮታዊ ነኝ ባይነት ማስቆም አልቻሉም፡፡ ትዕግስት ይባሱኑ ..የሥላሴ መልዕክተኛ ድንግል ማርያም ነኝ.. ማለት ጀመረች ይላሉ - ምንጮች፡፡
በዚህ አድራጐቷ የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ተቃውሞውን በማሰማት ከአካባቢው አባረራት፡፡ ትዕግስት በዚህ ጊዜ ወንጪ ገዳም እንደገባች የገለው ፖሊስ፤ ሀይለገብርኤል ከተባለው ተከታይዋ ሦስተኛ ልጇን እንደ ወለደች ይናገራል፡፡ ከወንድ ጋር ተገናኝታ እንደማታውቅ የምትናገረው ትዕግስት፤ ሦስቱንም ልጆቼን በመንፈስ ቅዱስ ነው የወለድኳቸው ባይ ናት፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቷም ይሄንኑ ይመሰክራል - ከእሷ ጋር ስጋዊ ግንኙነት ፈጽሞ እንደማያውቅና ሁለት ልጆቿን በመንፈስ ቅዱስ እንደወለደቻቸው በመናገር፡፡
ትዕግስት በወንጪ ገዳም ሳለች የሥላሴ መልዕክተኛ ነኝ ማለቷን - ገፍታ ቀጠለችበት፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ሌላ ጉድ መከሰቱን የሚናገሩ ምንጮች፤ እናቷ ወ/ሮ ባይሴ ኡዊሳ (በክርስትና ስማቸው ወለተ ሥላሴ) ነሐሴ 25 2000 ዓ.ም. ከቀኑ 9 ሰዓት ሞተው እንደተገነዙ፣ ከዚያም የዚያኑ ዕለት ከምሽቱ 4 ሰዓት ከሞት ተነሱ ተብሎ እንደተወራ ይናገራሉ፡፡ እናት ከሞት የተነሱት ከሰማይ የተላኩትን መልዕክት ለማድረስ እንደሆነ ገልው ..ወ/ሮ ትዕግስት ወይም በክርስትና ስሟ ምስለ ፍቅር ኢየሱስን ስሟት ተብላችኋል.. ካሉ በኋላ በነጋታው ተመልሰው እንደሞቱና ነሐሴ 27 2000 ዓ.ም. የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት እንደተፈመ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ግን መቃብራቸው ተከፍቶ እንዳረጉ ነው ልጃቸው ትዕግስት የተናገረችው፡፡
ነሐሴ 29 2000 ዓ.ም. ሌሊት ላይ ነጐድጓድ መብረቅ ሰምቶ ከጥበቃ ክፍሉ እንደወጣ የሚናገረው የገዳሙ የጥበቃ ሠራተኛ፤ የትዕግስት እናት (በክርስትና ስማቸው ወለተ ሥላሴ) መቃብር ላይ መላዕክት እንዳየ ለፖሊስ ገልል፡፡ በእጁ አብርቶ ይዞት የነበረው ባትሪ መጥፋቱንና መብረቁ ገፍትሮ እንደጣለው ለፖሊስ የገለው የጥበቃ ሠራተኛ፤ በድንጋጤ ወደ ክፍሉ ተመልሶ እንደገባ ተናግሯል፡፡ ሲነጋጋ ሁኔታውን ለማጣራት ወደ መቃብሩ ሲሄድ የወለተ ሥላሴ መቃብር ለሁለት ተከፍሎና መሃሉ ተሰንጥቆ፣ የአስከሬን ሳጥኑ ባዶ ሆኖ ማየቱን በሰጠው ቃል ገልል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትዕግስት ..የዓለም ፍጻሜ ደርሷል፤ ንስሀ ግቡ.. እያለች መስበክ እንደጀመረች ምንጮች ይናገራሉ፡፡
ሴትዮዋ የተቀበሩበት ስፍራ ታጥሮ በሰዎች እየተጐበኘ እንደሆነ የጠቆመው ፖሊስ፤ ሁኔታው የማጣራት ሥራ እንደሚፈልግም ይናገራል፡፡
በረቡዕ ቀን በሬና በግ አርዳ ነዋሪዎች በፆም ቀን ሥጋ እንዲበሉ ማስገደዷ ከነዋሪው ጋር ለተፈጠረው ግጭት መንስኤ ሲሆን፤ የፆም ቀን ቢሆንም አብርሃም ቤትም በሬ ተጥሎ ለሰዎች የመገበው ሐምሌ ሰባት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል በማለት ሐምሌ 7 2002 ዓ.ም. ነዋሪው ሥጋ እንዲበላ፣ ካልበሉ ግን ምድር ተከፍታ እንደምትውጣቸው ታስፈራራ ነበር ተብሏል፡፡ ሥጋውን የበላ ይማራል በማለቷ ግማሹ ነዋሪ ቢበላም ግማሹ አልበላም እንዳለ የጠቆሙ ምንጮች፤ በዚህም ምክንያት ትዕግስት ከአካባቢው ለቅቃ አዲስ አበባ እንደገባች ይናገራሉ፡፡
አዲስ አበባ ከተከታዮቿ አንዷ በሆነችው ሃና ብሩክ በተባለች ግለሰብ መኖሪያ ቤት (ሳር ቤት አካባቢ) ያረፈችው ትዕግስት፤ ከየት እንደመጡ ያልታወቁ 16 የሚደርሱ ህፃናትና ጐልማሶች አብረዋት ይኖሩ እንደነበር ታውቋል፡፡ ህፃናቱን ለልመና ተግባር ትጠቀምባቸው እንደነበር የጠቆመው ፖሊስ፤ እሷን ተከታይ እንደሆኑና ደረታቸውን በድንጋይ እንዲደልቁ ታደርጋቸው እንደነበር እንዳረጋገጠ አመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ ተከታዮቿ ራሳቸውን የማያውቁና ከትክክለኛ አዕምሯቸው እንደተለዩ የሚናገረው ፖሊስ፤ የሴትዬዋ ድርጊት የተጋለጠው ህፃናቱ ለጐረቤት ..እመብርሃን ናት፤ ደሟን እየቀዳች የክርስቶስ ደም ነው እያለች ትሰጠናለች.. ብለው ከተናገሩ በኋላ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በመጠቆም ወ/ሮ ትዕግስት ብርሃኑ በቁጥጥር ስር እንደዋለች ገልል፡፡
በወቅቱ ፍተሻ አለማካሄዱን የጠቆመው ፖሊስ፤ ህፃናቱ የት እንዳሉ እንደማያውቅና ምርመራ ላይ መሆኑን የገለ ሲሆን ከሦስት ዓመት በፊት ከተከታዮቿ አንዷ የነበረችው የ19 ዓመቷ ትዕግስት ያለው ለስምንት ቀን ያለምግብ በመቆየቷ፤ ደረቷን በድንጋይ እንድትደልቅና የተበጠበጠ ምንነቱ ያልታወቀ ቅጠል እንድትጠጣ በመደረጉ ህይወቷ እንዳለፈ ገልል፡፡ የወጣቷን አስከሬን በማውጣት የአሟሟቷን ሁኔታ ለማጣራት ከህክምና ባለሙያዎች ጋር እየተመካከረ እንደሆነም ፖሊስ አክሎ ገልል፡፡
ከወ/ሮ ትዕግስት ብርሃኑ ጋር በተያያዘ ትዳራቸው የፈረሰ፣ ንብረታቸውን ያጡ ግለሰቦች እንዳሉም የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡
አዲስ አበባ ቤቴል የተባለው ሰፈር ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ አለሚቱ ጉቱ በትዕግስት በደል እንደደረሰባት ቃሏን ለፖሊስ ሰጥታለች፡፡ ቤተሰቧቿ ወደ አምቦ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ የወሰዷት፣ ወ/ሮ ትዕግስት በበል ከህመምሽ ትፈውስሻለች በሚል እንደሆነ የተናገረችው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ከተጠመቀች በኋላ ከቲቢ ካንሰር ተፈውሰሻል ብለው ህዝብ ተሰብስቦ በቪዲዮ እንደተቀረች ለፖሊስ ገልጻለች፡፡
ከዚህ በኋላ ደግሞ ልጆቼንና ወርቄን ነጥቃኛለች የምትለው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ልጆችሽ የእኔ እንጂ ያንቺ አይደሉም መባሏን ትናገራለች፡፡ ..አንድ ቀን የትንሿን ልጄን ጉር ሳበጥር ለምን ነካሻት ተብዬ እስከምዝለፈለፍ ድረስ ተደብዳቤአለሁ.. ትላለች፡፡
ከእኔ የትም አታመልጡም ስለምትል ሁሉም ይፈራታል የምትለው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ተከታዮቿ ..እመቤታችን ናት አምልኳት.. እንደሚሉ ትናገራለች፡፡ ..በምስል ታመልካላችሁ፤ ይኸው በአካል መጥታለች አምልኳት.. ይሉናል ብላለች፡፡ በየቀኑ ፆም አለ፤ በቀን አንዴ ንፍሮ እንበላለን ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ፆሙ የአዋቂ ብቻ ሳይሆን ከስድስት ወር ጀምሮ ያለ ህፃንም እንዲፆም ይደረጋል - ለሦስት ቀን ጡት አይሰጠውም ብላለች፡፡
ወ/ሮ ትዕግስት ትምህርት ሃጢያት ነው በሚል አቋም ልጆች እንዳይማሩ እንደምታደርግ አለሚቱ ለፖሊስ ተናግራለች፡፡
የ12 ዓመት ልጄን ከዚህ እንግልት ለማዳን እንጥፋ ብዬው ነበር፤ እሱ ግን ፈርቶ እምቢ አለኝ የምተለው - አለሚቱ፤ የባሰው መከራ የመጣው ግን የ3 ዓመት ልጄ ለ3 ቀን ያለ እህል ውሃ ፆም ፀሎት መያዝ አለበት ስትላት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ትልቁ ልጄ አሻፈረኝ ስላለ ሌላ ሙከራ ባደርግ ይገድሉኛል ብዬ ትንሿን ልጇን ይዛ እንደጠፋች ተናግራለች፡፡ የወንድ ልጇ ነገር ያላስቻላት ወ/ሮ አለሚቱ፤ ተመልሳ ወደ አምቦ መሄዷን ትናገራለች፡፡
ሆኖም ሰው ሁሉ ስለጠላቸው ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል ተብላ መመለሷንና ልጇን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማግኘቷን ገልጻ ለሳምንት ያህል አብሯት ከቆየ በኋላ እንደጠፋ ገልጻለች፡፡ ፖሊስ ልጇን ለሁለተኛ ጊዜ አግኝቶ የሰጣት ቢሆንም ተስማምተው ሊኖሩ እንዳልቻሉ እናት ትናገራለች፡፡ እኔን እንደ እናቱ ሳይሆን እንደ ጠላት ነው የሚያየኝ ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ..ማርያምን ከሰሻት እኔ ካንቺ ጋር አልኖርም.. ይላት እንደነበር ገልጻለች፡፡ ልጄ ..እኛ ምድራዊ አይደለንም፤ ሰማያዊ ነን.. እያለ እሷ የምትናገረውን ሲደግም ነገሩ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ስለገባኝ ወደ እነሱ እንዳይመለስ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል የምትለው እናቱ፤ አሁን ትንሽ ቢሻሻልም፤ እሷን ግን እንደጠላት እንደሚመለከታት ትናገራለች፡፡ ልጄ ጤነኛ አይደለም ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ንብረቴን በሙሉ አጥቼአለሁ ከምንም በላይ የሚጽተኝ ግን ልጄን ማጣቴ ነው ብላለች - እንባዋን እያፈሰሰች፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት አበራ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ስትሆን ጉዳይዋ ወደ ፍርድ ቤት ተልኮ በጊዜ ቀጠሮ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ወ/ሮ ትዕግስት ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ..የሥላሴ መልዕክተኛ ነኝ እኔ ከወንድ ጋር አልተኛሁም፤ ተርፌሳም ማርያም ዮሴፍን ይጠብቃት እንደነበር ጠባቂዬ ነው፤ ሦስት ልጆች ቢኖሩኝም በመንፈስ ነው የወለድኳቸው፤ ይህንን ሁሉ ያደረኩት ሥላሴዎች አዘውኝ ነው፤ አላጠፋሁም.. ብላለች፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_content&view=article&id=790%3A2011-08-13-09-13-55&catid=76%3Ahot-topic&Itemid=994 በተጨማሪ ፖስት ያደረግነውን ቪዲዮ ይመላከቱ See part 1 http://dekikenabute.blogspot.com/2011/08/blog-post_7994.html?spref=fb part 2 http://www.facebook.com/video/video.php?v=137399669685908&comments&notif_t=video_commen    
part 3 http://www.facebook.com/video/video.php?v=137814382977770&comments&ref=notif&notif_t=video_comment 

Tuesday, August 23, 2011

መለየትን የሚወድ ምኞቱን ይከተላል. ምሳሌ ም .18 ቁ. 1


መለየትን የሚወድ ምኞቱን ይከተላል..
ምሳ ም 18 ቁ 1
"የሞት አያት ማነው?" ብለው በአንድ ወቅት መምህራችን ጠየቁን ሁሉም ለመመለስ አጁን አወጣ፡፡ በጣም ተደነኩ አኔ ግን "ደሞ ለሞትም የዘር ሀረግ አለው እንዴ ?"ብዬ መልሱን ለመስማት ቸኮልኩ፡፡ ብዙዎቻችሁ መልሱን እንደምታውቁት እገምታለሁ፡፡ ግን መልሱን ከማወቃችሁ በፊት ለዚህ ጥያቄ ምን አይነት ምላሽ ትገምቱ ይሆን? አኔ መልሱ እስኪመለስ ባለው ጊዜ በጣም ብዙ ነገር አሰብኩ፡፡ አኔ ካሰብኩት አንዱም መልስ አልነበረም፡፡
በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ምዕ 1 ቁ 12-15
"በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።  ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።  ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።"
ንግዲህ የሞት አያቱ ምኞት ነው ማለት፡፡ መጽሐፍት አንደሚነግሩን
ዘፍ ም 3 ቁ 3-6"… እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።
ሔዋን ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ አየች(ተመኘች) ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ወለደች ማለትም ሔዋን ቆርጣ በላች (ሕገ እግዚአብሔርን አፈረሰች) የኃጢአት ደሞዙ (ልጅ) ሞት ነውና ሞት ተፈረደብን፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሞቱ ሞትን ሽሮልናል፡፡
አሁን በዚህ ዘመን ምኞታቸውን በመከተል መለያየትን በቤተክርስቲያናችን ለመፍጠር የሚጥሩ አንድና ሁለት አይደሉም፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳለ የራሳቸውን ክብር አንጂ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ምናቸውም ያልሆነ በአጠቃላይ ምኞታቸውን ብቻ የሚከተሉ አባቶችን ከራሳቸው አሳንሰው ራሳቸውን ከፍ አድርገው የቤተክርስቲያን ልጆች እኛ ብቻ ነን የሚሉ (------እኔን ወለደች እገሌን ወለደች -------) ናቸው፡፡ "በልቡ ያለውን ሁሉ መግለጥ ብቻ ይወድዳል እንጂ" ምሳ ም 18 ቁ 2
አነዚህ ሰዎች በጣም የሚገርም ነገራቸው "ለካ ትወዱናላችሁ ለካ ታከብሩናላችሁ ለካ እኛ ብንወድቅ ይህ ሁሉ ሕዝብ ይወድቃል" እያሉ ህዝቡን በምላሳቸው በቃ ምን አለፋችሁ ሁሉም ነገር ምላሳቸው ላይ ነው ያለው፡፡ የቤተክርስቲያንን ፍቅር፤ የሕዝብ ፍቅር ----ወዘተ በምላሳቸው ምላስ ብቻ፡፡ ግን በተጨማሪ ምላሳቸው ከዚህ የተለየም ነገር አለው፤ ስድብ ፡፡ አትሳደቡ ብለው ግን አስተምረውን ያውቃሉ፡፡ ደሞ የት እንደሚሳደቡ ታውቃላቸሁ አውደ ምሕረት ላይ ቆመው፡፡ ምሳሌ (የንፍሮ ቀቃይ ልጅ፣ ……………………..) ከዚህም በላይ እኔ በጣም በእውነት እላችኋለሁ በጣም አዝናለሁ በአውደ ምሕረት ላይ "የጥፋት ርኩሰት ቆሞ ስታዩ ያኔ ሰሚው ያስተውል" 
አነዚህ ሰዎች እውነት አውደ ምሕረት ላይ ራሳቸውን ሳያርሙ፤ የሰደቡትን ሕዝብ ይቅርታ ሳይጠይቁ፤ ሳይማሩ(መቼም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን ሳያውቁ እንደ ሚያውቁ ሆነው ሲያስተምሩ ሰምተናል ብዬ ነው) ማስተማር አለባቸው ትላላችሁ????
                                                የገዛ ምኞታችንን ከመከተል
የአግዚአብሔርን መልካም ፈቃድ እንድናውቅ
              ፈቃዱንም እንድንተገብር አግዚአብሔር ይርዳን!
የቅዱሳን አባቶቻችን ጸጋ በረከታቸው
ጥርጥር የሌለባት ሃይማኖታቸው
ድል የማትነሳ እምነታቸው
ከአኛ ከሁላችን ጋር ትሁን አሜን!!!!!!!!!

Friday, August 19, 2011

ይቅርታና ይቅር ባይነት

ይቅርታ ወይም ይቅር ባይነት የሰው ልጅ በዚህ ዓለም በሚኖርበት ወቅት በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስሮች ወይም ግንኙነቶች አማካኝነት ከሌሎች የማኅበረሰቡ  ክፍሎች ጋር ለሚኖረው ጤናማ የኑሮ ጥምረት ትልቅ ድርሻ አለው ብዬ አምናለሁ። ይቅር መባባል ያለፈ በደልን አጥቦና አስወግዶ ለቀሪው ህይወት አዲስ ልቡናን በመፍጠር ግንኙነታችንን ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል። በአንድ ወቅት በታሪክ አጋጣሚ ተበዳድለው፣ ተቀያይመው፣ ተኮራርፈው ከዚያም ባለፈ ደም ተቃብተው እና ለቂም በቀል ሌት ተቀን በሃሳብም በግብርም ይሯሯጡ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በልቡናቸው የተቋጠረውን የመጠፋፋት ሕልምና ዕቅድ ወደ ጎን ትተው  አንዱ ካንዱ በጋብቻ እስከመጣመርና አንዱ ላንዱ ዋስ ጠበቃ እስከመሆን ያደርሳቸዋል። በዚሁ መልካም አጋጣሚ ምክንያትም ሊጠፋ የነበረው ሕይወት፣ ሊፈስ የነበረው ደም እና ሊጎድል የነበረው አካል ከጥፋት፣ ከመፍሰስና ከመጉደል ይድናል።


ከዚህም ባለፈ ቂም በቀል በይቅርታ እስካልተደመደመ ድረስ ጥፋቱ መቋጫ የለውም። አንዱ ላለፈ በደሉ አዲስ በደል ሲፈፅም ሌላኛውም አፀፋውን ሲመልስ የሁለቱም ወገኖች በምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ መጠፋፋቱ ይቀጥላል። እንዲህ ዓይነቱ ለይቅርታ ቦታ አለመስጠት በተለይ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ በእኛ በኢትዮጵያውያን ይብሳል። ምክንያቱ ምን ይሆን? በምጣኔ ሃብት አለማደጋችን፣ በቴክኖሎጂ አለመበልፀጋችን ወይም ገና ያልደረስንበትና ያልተማርነው ዘመናዊ ትምህርት ይኖር ይሆን? ትልቁ መንስዔ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል እንዳልሆነ የምንገነዘበው እነዚህ ምክንያትች ሞልተው የተትረፈረፉላቸው ወገኖቻችን ይባስ ብለው የችግሩ ሰለባ እነሱ መሆናቸው ነው።

ያደግንበት ማኅበረሰብም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በእትንኩኝ ባይነትና ክንዴን ሳልንተራስ እንዴት እደፈራለሁ? አስተሳሰቡ በደንብ አድርጎ አጥምቆናል። ገና ከእናታችን ማኅፀን ከመውጣታችንም ደም መላሽ ብሎ ስም ያወጣልናል። አንደበታችን እማማ አባባ ማለት ሳይጀምር በቂም በቀል ዲፕሎማ ከቤተሰባችን እና ከአካባቢያችን በከፍተኛ ማዕረግ እንመረቃለን። ከዚያ በኋላ ልክ ግብፃውያን እናቶች ልጆቻቸውን አባይ ሕይወትህ ነው እያሉ እንደሚያሳድጉት ሁሉ ለእኛም የስማችንን ትርጓሜ ከወደፊቱ ስራችን ዕቅድ ጋር እየተነገረን እናድጋለን። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝብን እናዝናናበታለን በሚል ሽፋን የሚወጡ ዘፈኖችም የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው። የአንድን ግለሰብ አስተሳሰብ ለመግለፅ እንዲሁም ለግጥሙ ቤት መድፋት እንጂ ጭብጡ በማኅረሰቡ ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ባለማስተዋል የሚዘፈኑ ዘፈኖች አሉ። “ተበድዬስ ይቅርታ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ” የሚል ዘፈን ሲያዳምጥና አብሮ ሲያንጎራጉር ያደገ ሰው ለይቅርታ ያለው ቦታ ቢያንስ ኸረ እስከ ጭራሹም ባይኖረው ምን ይደንቃል?

ሁላችንም እንደምናስታውሰው በጀግኖች አባቶቻችን ቆራጥ ተጋዳይነት ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሚተርፍ የነፃነት ፋና በዓድዋ ተራሮች ተንቦግቡጎ ባልጠበቀውና ባላሰበው መልኩ ድል የተደረገው የኢጣልያ መንግስት ይህንን በዓለም አቀፍ አደባባይ የውርደት ሸማ ያለበሰውን የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ቂም ለመወጣት በተጠቀመው የመርዝ ጋዝ እጅግ ብዙ ወገኖቻችን በመሪር ስቃይ አልፈዋል። እስቲ እነዚህን የነፃነታችን አምድና ለዛሬው እኛነታችን የሕይወትን መስዋዕትነት ከፍለው ስማቸውን በልባችን ፅላት ላይ በወርቅ ማኅተም ያተሙትን ወገኖቻችንን አንድ ጊዜ ቆም ብለን እናስባቸው። 

በዚያን ጊዜ እነደዚያ ያለውን የጭካኔ ርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘውን አካል ብናገኘውና እጅና እግሩ ታስሮ ፊት ለፊታችን ቢቀርብልን ምን ዓይነት ርምጃ ይሆን የምንወስድበት? እንደው የትኛውን የቅጣት ዓይነት ብንቀጣው ነው አንጀታችን ቅቤ የሚጠጣው? ምን ዓይነት የአገዳደል ስልት ብንጠቀምና ብንገድለው ነው  ያለፈውን የወገኖቻችን ሕይወት፣ የጎደለውን አካላቸውን እና የፈሰሰውን ደማቸውን ዳግም ማግኘት የምንችለው? ቁርጥርጥ አድርገን ብንፈጨውና ወደ አፈር ብንቀይረው ከዚያም ዳግም እንደ ጭቃ አብኩተን ሰውዬውን ሰርተነው እና ሃይሉ ኖሮን እስትንፋስ እንዲኖረው አድርገን እንደገና ብንቆራርጠው ይህንንም ሂደት ሕይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን ቁጥር ብንደጋግመው ስንቶቹን ይሆን ዳግም በሕይወት የምናገኛቸው? ምንም። እርሱ በከፈተው የክፋትና የጭካኔ ጎዳና አብረነው እንድንጓዝ እና እርሱ ለሰራው ጥፋት በሚጠየቅበት ቦታ ብቸኝነት እንዳይሰማው ከማድረግና ከሚከፈለው ክፍያ ተቋዳሽ ከመሆን ያለፈ ጠቀሜታ የለውም።

ታድያ ቂም በቀሉ ፋይዳው ምንድነው? የመንፈስ እርካታ ይገኝበት ይሆን? በቂም በቀል ደስታና እፎይታን ብሎም እርካታን የሚያገኘው መንፈስ እንዴት ያለው መንፈስ ነው? በእውነት ነፍሳችን በእንደዚህ ያለ ድርጊት ደስታን ታገኝ ይሆን? በጭራሽ። ቂም በቀል ጊዜያዊ የሆነ እርካታን ለስጋችን ይሰጠው ይሆናል እርሱም ቢሆን ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ይፀፀታል። ያጣሁትን መልሼ ላላገኝ ይህንን ማድረጌ ምን ጠቀመኝ? ለምንስ የሰነፎችን መንገድ ተከተልኩኝ? እያለ ራሱን መውቀሱ አይቀሬ ነው።  በደልን በበደል፣ ክፋትንም በክፋት፣ ተንኮልንም በተንኮል እንሸፍናለን በሚል የዋህ አስተሳሰብ ታስረን የነገሮችን ውል ከማጥፋት ይልቅ ጥፋትን ተራርሞ ክፍተትን በይቅረታ መሙለቱ የታላቅነትና የአስተዋይነት ብሩሕ ምልክት ነው። ይህ ይቅርታና ይቅር ባይነት መገኛው የት ይሆን?

እንደ እኔ አመለካከት ይቅርታ እና ይቅር ባይነት ምንጩ መንፈሳዊ ሕይወት ነው። ምንም እንኳን ይቅርታ መደራረግ ለስጋዊ ኑሯችንም ታላቅ ጠቀሜታ ቢኖረውም ዋናውና ከዚህ የሚበልጠው ግን መንፈሳዊው ዋጋ ነው። ይህንን መንፈሳዊ ዋጋ ያገኝ ዘንድ ዘወትር የሚተጋ ሰው ልቡናው ለይቅርታ የፈጠነ ነው። በዚህ ምድር በበዳዩ ከተበደለው በደል ይልቅ በሰማይ የሚያገኘው ክብር ሚዛን ይደፋለታል። እዚህ ላይ ግን ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን ነገር አለ። ይቅር ባይነት ቀላል አይደለም እንደማንኛውም ክብርን እንደሚያጎናፅፍ ተጋድሎ ሁሉ እርሱም ከፍተኛ ተጋድሎ ያሻዋል። በአፋችን ለመናገር እንደሚቀለው ያህል ለመተግበሩ ቀላል አይደለም። ይቅር ለማለት ስናስብ ብዙ ፈተናዎች ፊታችን ይጋረጣሉ። ፈተናው ከራስ ይጀምራል የቤተሰብ ፈተናም አለው እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖም አለው። እነዚህን ፈተናዎች በድል አድራጊነት መወጣት የሚችል ሰው ነው ይቅር የሚለው እና ሰማያዊውን ክብር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኘው።

ቁርሾን በሆድ ይዞ ዘወትር መበላላትን፣ መጠፋፋትን እና ልኩን/ለኳን አሳያታለሁ ባይነትን የዘወትር መገለጫው የሆነውን ሰጋችንን ሰማያዊውን ተስፋ አሻግራ ለምትመለከተው ነፍሳችን ስናስገዛ መንፈሳዊነት በሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደተለኮሰ ሻማ ከሩቅ ያበራል። የዚያን ጊዜ የበደሉንን አካላት መጥተው ይቅርታ እስኪሉን ሳንጠብቅ አስቀድመን ይቅርታን እናደርግላቸዋለን። የሰማያዊው ክብር ባለቤቶች መሆናችንን እናውቃለንና ይቅርታውን ባደረግን ወቅት ከመቼውም ይበልጥ ውስጣችን በሐሴት ይሞላል። የሰላም እንቅልፍም እንተኛለን።

ቸር ያሰማን፤ አሜን።

Thursday, August 18, 2011

በዚህ ዘመን ቅድስት ድንግል ማርያም በስጋ ተገለጠች ቢባሉ ምን ይላሉ?

አይን የማያየው የለም ጆሮም የማይሰማው የለም
በዚህችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የዋሓንን አማኝ በማሳት በማታለል የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ እና ስርአት ለማጥፋት የሚጥሩ ብዙ የዋህ እንዳሉ የማይካድ እውነታ ነው ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ከውጪ ያለችበት ከፍተኛ ፈተና ከፊት ተጋርጦ ሳለ እዚሁ በየገዳማቱ በየአድባራቱ ያሉትን የዋሀንን በፈለጉት ሀሳብ በመስበክ ሕዝቡን እያሳቱ እንዳለ ይህ እውነተኛ ምስክር ነው
  •        ማርያም በዚህ ዘመን ጌታን ለመውለድ ተገለጠች ቢባሉ ምን ይላሉ?
  •          እንደ አይሁድ ገና ጌታ ይወለዳል ቢባሉስ? 
  •      መለኮት ግንቦት 1/1999 ተፀንሶአል ይህንንም በ3 ቀን ሱባኤ ጠይቁ ቢባሉስ?
·         አረ ምኑ ቅጡ ሁሉንም ያድምጡት
በዚህ አይነት መልኩ ደጋፊ ማፍራት ይቻላል? 
see part 2 ተጨማሪ ከፌስ ቡካችን ያድምጡ ይህንም ይጫኑ
see part 3  ተጨማሪ ከፌስ ቡካችን ያድምጡ ይህንም ይጫኑ

ደቂቀ ናቡቴ

አክዓብም ናቡቴ በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው ናቡቴም አክዓብን የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው እስከ ሞሞትም በቃ ለርስቱ የናቡቴ ልጆችም ዛሬ እርስታችንን ተዋህዶን ለእነ አድሳት ባዮች አንሰጥም እስከ ደም ጠብታ እንከፍላለን ሲሉ ነው

አባ ሙሴ ጸሊም


አባ ሙሴ ጸሊም በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አስቀድሞ በውንብድና ኑሮ ሕይወቱን ይገፋ ነበር፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል፡፡እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ ፤ በሥራውም ኃይለኛ ነበር፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ፤ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ፡፡ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ
በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ፤ ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው፡፡ ያንጊዜም ተነሳ ሰይፉንም ታጥቆ ወደአስቄጥስ ገዳም ሄደ ፤ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው ፤ አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው ፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደአባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው፡፡ እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሰህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ
የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኮሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙ እና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ፡፡፡፡በኋላም በገዳመ አስቄጥስ የገዳሙ አበምኔት የነበረው የአባ ኤስድሮስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በአባ መቃርዮስ ምክር ወደ ጴጥራ ሂዶ በተባሕትዎ መኖር ቀጠለ፡፡ ከገድሉ ብዛት የተነሳ አረጋውያን መነኮሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውሃ መቅጃዎቹን ወስዶ ውሃ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር፡፡ ውሃው ከእነርሱ ሩቅ ነበርና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም በበአቱ እያለ የፈቲው ፆር ያሠቃየው ነበር፡፡ ፈተናውን ተቋቁሞ በበአቱ መቀመጥ ስላልቻለ ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ኤስድሮስ ዘንድ ሄደና ‹በበኣቴ መቀመጥ አልቻልኩም› አለው፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደ በኣቱ ተመልሶ በዚያው እንዲጸና መከረው፡፡ ሙሴ ግን ‹ፈጽሞ አልችልም› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ሙሴን ይዞት ከገዳሙ ቅጥር ውጭ አወጣው ከዚያም ወደ ምዕራብ አዞረውና ‹ተመልከት› አለው፡፡ በዚያ አቅጣጫ የአጋንንት መንጋ ለወረራ ሲዘጋጁና ሲንጫጩ አሳየው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ምሥራቅ እንዲመለከት አደረገውና እልፍ አእላፍ መላእክት ብርሃን ተጐናጽፈው አሳየው፡፡ ከዚያም ‹እነዚህ የብርሃን መላእክት ቅዱሳንን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ ናቸው እነዚህ ርኩሳን አጋንንት ደግሞ ቅዱሳንን ለመፈተን የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የብርሃን መላእክት ኃይል ከአጋንንት ኃይል ይበልጣሉና ጸንተህ ተጋደል› ሲል መከረው አባ ሙሴም ወደ በኣቱ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በገዳመ አስቄጥስ እያለ ከገዳማውያን አንዱ ጥፋት ሠራና ማኅበሩ ለፍርድ ተሰበሰበ፡፡ አባ ሙሴ ግን በጉባኤው ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ካህኑ ተልኰ ‹ና. ሁላችንም አንተን እየጠበቅን ነው› አለው፡፡ አባ ሙሴም በሚያፈስስ ከረጢት አሸዋ ሞልቶ ያንንም በጀርባው ተሸክሞ ከኋላው እያፈሰሰ ወደ ጉባኤው አመራ፡፡ ጉባኤተኞቹ ተገርመው ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹የእኔ ኃጢአቶች በኋላየ እንደዚህ አሸዋ በዝተው ይፈሳሉ፤ ነገር ግን ላያቸው አልቻልኩም ዛሬ ግን በሌላው ላይ ለመፍረድ መጥቻለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ዝም አሉ፡፡ ያን ወንድምም በይቅርታ አለፉት፡፡
በሌላ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ያሉ መነኰሳት ተሰበሰቡና የአባ ሙሴን ትዕግሥት ለመፈተን ሲሉ “ይህ ጥቁር መነኩሴ ለምን እዚህ መጣ “ ብለው ተናገሩት፡፡ እርሱም ዝም አለ፡፡ ጉባኤው ሲበተን “አባ ክፉ ስንናገርህ ምንም ሐዘን አልተሰማህም ነበርን ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ተሰምቶኛል፣ ነገር ግን እንዳልናገረው አንደበቴን ተቆጣጠርኩት” አላቸው፡፡
በአንድ ወቅት በገዳመ አስቄጥስ ጾም ታወጀ፡፡ በዚያ ሳምንት አባ ሙሴን ለማየት ከግብጽ ወንድሞች መጡ፡፡ አባ ሙሴም በእንግድነት ተቀበላቸውና ምግብ ያበስልላቸው ጀመር፡፡ የእሳቱን ጢስ የተመለከቱ ጐረቤቶቹ “አባ ሙሴ ትእዛዝ አፍርሶ ምግብ ያበስላል” ብለው ለገዳሙ ሓላፊዎች ተናገሩ፡፡ ሓላፊዎቹም ‹አሁን ተውት ሲመጣ እኛው ራሳችን እናናግረዋለን› አሏቸው፡፡ ሓላፊዎቹም አባ ሙሴን ጠርተው ለምን ምግብን እንዳበሰለ ተረዱ፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ማኅበሩ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በአደባባይ ‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡
አንድ ጊዜ የአካባቢው ገዥ ስለ አባ ሙሴ ዝና ሰምቶ ያየው ዘንድ ወደ ገዳመ አስቄጥስ መጣ፡፡ ይህን የሰማው አባ ሙሴ ሸሽቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡ በመንገድም ላይ የገዥው መልእክተኞች አገኙትና ‹እባክህ አባ ሙሴ የት እንዳለ በኣቱን አሳየን› አሉት፡፡ ‹ከርሱ ምን ትሻላችሁ፤ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው› አላቸው፡፡ ይህን የሰማው የአካባቢው ገዥ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጣና የሆነውን ሁሉ ለአገልጋዮች ነገራቸው፡፡ ‹ብዙ ሰዎች ስለ አባ ሙሴ ሲያወሩ ሰምቼ ለማግኘት መጥቼ ነበር፤ በመንገድ ላይ ያገኘነው አንድ አረጋዊ ሰው ግን የአባ ሙሴ በኣት የት እንደሆነ ስንጠይቀው ከርሱ ምን ትሻላችሁ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው አለን› ብሎ ነገራቸው፡፡ አገልጋዮቹም በጣም ተናደዱና ‹ምን ዓይነት አረጋዊ ሰው ነው ስለ ቅዱሱ ይህን የሚናገር› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ትልቅ፣ ጠቆር ያለ፣ አሮጌ ልብስ የለበሰ ነው› አላቸው፡፡ አገልጋዮቹም ተገርመው ‹ይህማ ራሱ አባ ሙሴ ነው፤ ይህን ያለህ ሊያገኝህ ስላልፈለገ ነው› አሉት፡፡ የአካባቢው ገዥም ከአባ ሙሴ ሁኔታ ከንቱ ውዳሴን ስለ መሸሽ ትልቅ ትምህርት ተምሮ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በኣት ሠርቶ ወደ ጴጥራ ሲሄድ በአካባቢው ውኃ ስላልነበረ ተጨንቆ ነበር፡፡ አንድ ድምፅ ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› አለው፡፡ ስለዚህም በዚያ መኖር ጀመረ፡፡ አንድ ቀን በጴጥራ እያለ አበው ሊጐበኙት መጡ፡፡ የነበረችው ውኃ ጥቂት ነበረችና በርሷ ምግባቸውን አበሰለ፡፡ የሚያጠጣቸው ግን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ እየወጣ ውኃ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር፡፡ በመጨረሻ ዝናብ ዘነበና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ሁሉ ሞላቸው፡፡ እነዚያ አባቶችም ‹ትወጣና ትገባ የነበረው ለምን እንደሆነ እባክህ ንገረን› አሉት፡፡ ‹እናንተ በእንግድነት ስትመጡ ውኃ አልነበረኝም፣ ስለዚህ ያንተን አገልጋዮች ወደ እኔ ልከሃቸዋል፣ ነገር ግን ውኃ የለኝም፣ ስለዚህ እባክህ ውኃ ስጠኝ እያልኩ እግዚአብሔርን ለመለመን ነበር› አላቸው፡፡
አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ሙሴም ‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት፡፡› አለው፡፡ ‹ሌላ አይጠበቅበትምን?› ሲል ያ ወንድም ጠየቀው፡፡ ‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ሓላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብጽን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም› አለና መለሰለት፡፡ ያም ወንድም ‹ምን ማለት ነው?› አለው፡፡ ‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ‹ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡› በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሓሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው፡፡
አንድ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ወንድሞች አብረውት እያሉ አባ ሙሴ ‹ተመልከቱ በርበሮች ገዳማችንን ሊያጠፉ እየመጡ ነው፡፡ ተነሡና ሽሹ› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ‹አባ አንተስ አትሸሽምን?› ሲሉ ጠየቁት፡፡ አባ ሙሴም ‹እኔማ ይህችን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ፡፡ ጌታ በወንጌል ‹ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ› ያለው ቃል (ማቴ. 25.52) ይፈጸማል፡፡› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹እኛም አንሸሽም፣ አብረን እንሞታለን እንጂ› አሉት፡፡ አባ ሙሴም ‹ያ ለእኔ ረብ የለውም፤ ሁሉም ሰው ለየራሱ ይወስን› ብሉ መለሰላቸው፡፡ በዚያ ለነበሩት ሰባት ወንድሞች ‹በርበሮች ወደ ገዳሙ ደጅ እየደረሱ ነው› ብሎ ነገራቸው፡፡ ወዲያውም በርበሮቹ ደርሰው ገዳማውያኑን በሰይፍ መቷቸው፡፡ ከሰባቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሸሸና በተቆለለው ሰሌን ውስጥ ተደበቀ፤ ወዲያውም ሰባት አክሊላት ሲወርዱላቸው ተመለከተ፡፡
የአባ ሙሴ ጸሊም በረከት ይደርብን አሜን
ዋቢ ስንክሳር ሠኔ 24
በበረሓው ጉያ ውስጥ

የተለያዩ ጊዜ በጋሻው የፈጸማቸው ስህተቶች


Friday, August 5, 2011

የዐሥርቱ ትዕዛዛት ዓላማ





ዐሥርቱ ትዕዛዛት የተሰጡት በሚከተሉት ዓላማዎች ነው፡፡ ይኸውም፡-

1. ከግብጽ ምድር ስላወጣቸው ውለታውን እንዲያስቡ
2. ወደ ፊት በአረማዊያን መካከል ሲመላለሱ ከኃጢአት እንዲቆጠቡ
3. መንፈሳዊ አካሄዳቸው ምን ምን አቅጣጫ መከተል እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡

የዐሥርቱ ትዕዛዛት አከፋፈል

የክርስቲያን ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞበታል ካለ በኋላ ከዐሥርቱ ትዕዛዛት የተወሰኑትን በመጥቀስ ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ መሆኑን በግልጽ ይነግራል፡፡ ሮሜ 13፡8-10 ታዲያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረ ፍቅር በሁለት ይከፈላል፡፡ ማቴ 22፡34-41

1 ፍቅረ እግዚአብሔር 2 ፍቅረ ቢጽ

1. ፍቅረ እግዚአብሔር ከአንደኛ ትዕዛዝ እስከ ሦስተኛው ያሉት ሲሆኑ እግዚአብሔርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

2. ፍቅረ ቢጽ ከአራተኛ ትዕዛዝ እስከ አሥረኛ ትዕዛዝ ያሉት ሲሆኑ በለእንጀራን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአዎንታዊና በአሉታ ከመነገራቸው አንጻር በሁለት ይከፈላሉ ይኸውም፡-
1. ሕግ በአሉታ የተነገሩ /አታድርግ/
2. ትዕዛዝ በአዎንታ የተነገሩ /አድርግ/

ከዚህም ሌላ ከአፈጻጸማቸው አንጻር ሲታዩ በሦስት ይከፈላሉ፡፡

1. በሐልዮ የሚፈጸሙ 1፣3፣4 እና 9 በሐሳብ
2. በነቢብ የሚፈጸሙ 2፣ 8 በመናገር
3. በገቢር የሚፈጸሙ 5፣6፣7 እና 10 በሥራ ናቸው፡፡

ብሂለ አበው

0 ለተወሰን ጊዜ ለሀይማኖት መከራከር፤ጠበቃ መሆን፤መዋጋት ብሎም መሞት አይከፋም ሁልጊዜ ለሀይማኖት መኖር ግን ከሁሉ የበለጠ መስዋእትና ክብር ያለው ህይወት ነው፡፡

o የረብዑ ምግብ ለሀሙስ የአርብ ምግብ ለቅዳሜ ይጠቅማል ነገር ግን የማክሰኞ ምግብ ለረብዑ አይጠቅምም የሀሙስ ምግብ ለአርብ አይሆንም የነፍስና የስጋ ነገርም እንዲሁ ነው፡፡


o የነፍሳችን ነገር ትተን የስጋችንን ብቻ የምናደልብ ከሆነ ነፍስን በስጋ መቃብር እየቀበርናት መሆኑን አንርሳ

o አንድ በርሜል ወተት በአንድ ጠብታ ኮምጣጤ የበጣጠሳል የብዙ ጊዜ ተጋድሎንም ጠብታ የሀጢያት ኮምጣጤ ያበላሸዋል


o ራስህን በሀሰት አትውቀስ፡፡ራስህ መክሰስ ትህትና አይደለም፡፡ ታላቅ ትህትና ሰዎች ሲወቅሱህ መታገስ ነው

o ትዕቢት ሰይጣን ያለመው ጦር ነው

o ትህትና ህፀፅን የምታስታውቅ መስታወት ናት

o ክርስትና ማለት የሰውን ሸክም መሸከምና እስከሞት ድረስ መፅናት ማለት ነው

o በባልንጀራው ላይ ክፋትን የሚያስብ ሰው ያችው የሚያስባት ክፋት ራሱን ትጎዳዋለች፡፡ በየትና ምን ጊዜ እደምትጥለው ግን አያውቅም

o ስንፍናውን ወደጥበብ፤አላዋቂነቱን ወደእውቀት ፤መጥፎ ጠባዩን ወደበጎነት የሚመልስ ሰው ብርቱ ነው

o ፀሎት ገንዘብን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ገንዘብ ግን ፀሎትን አያመጣም፡፡

ብሂለ አበዉ


• ‹‹እግዚአብሔር ሆይ አፈርና ትቢያ ሆኜ ሳለ ጻድቅ አድርገው ከሚቆጥሩኝ ሰዎች አድነኝ››
አባ እንጦንስ
• ‹‹ፍጡራንን መርምሮ ማወቅ ካልተቻልን ሁሉን የፈጠረ እርሱን መርምሮ ማወቅ እንደምን ይቻልናል››
ቅዱስ አትናቴዎስ
• ‹‹ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ የክርስቶስንም ፀጋና ክብር ሳይፈተኑ ማግኘት አይቻልም የዚህ ዓለም ፈተናና እሳት ቶሎ ያልፋል ይጠፋል ኃጢያተኞች የሚገቡበት የገሀነም እሳት ግን ለዘላለም እንደ ነደደ ይኖራል››
ቅዱስ ሚናስ
• ‹‹በማንም ላይ ክፈትን አትስሩ አትፍርዱ ይህንን ከጠበቃችሁ ርስቱን ትወርሳላችሁና››
ታላቁ አባ መቃርስ
• ‹‹ብዙ ጊዜ ብዙ እናገራለሁ በመናገሬም አዝናልሁ በዝምታዬ ግን ያዘንኩበት ጊዜ የለም››
ቅዱስ አርሳንዮስ
• ‹‹ቤተክርስትያን መጠጊያችን ነች ቤተክርስትያን የኖኅ መርክብ ነች በውስጧ እንጠለላልን ከውጭዋ ግን ማዕበልና ቀላያት ተከፍተዋል››
ቅዱስ እንድርያስ
• ‹‹ልባችንን ጠፊና በስባሽ ከኾነው ከምድራዊው ምኞት አርቀን ከበደል በንስሐ ነጹሕ ካደረግነው በጸጋ መንፈስቅዱስ የተሞላን እንሆናለን››
አባ አብርሃም መፍቀሬ ነዳያን
• ‹‹ስጋዊ ፍላጎቶችን ማሸነፍ ለአክሊለ ህይወት የሚያበቃ ሰማዕትነት ነው››
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
• ‹‹የቤተክርስቲያን ህይወት በመስቀል ላይ ስለሆነ ፈተና ይበዛበታል ስለዚህ ከግል ህይወታችሁ ይልቅ የቤተክርስቲያናችሁን አቋም አጠንክሩ››
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
• ‹‹ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ፀሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው፡፡ እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትፀልይ እደር››
ቅዱስ ይስሀቅ ሶርያዊ
• ‹‹ኃጥያታችንን እኛ እያሰብን የምንፀፀት ከሆነ እግዚአብሔር ይረሳልናል ኃጥያታችንን እኛ እረስትን የምንፅናና ከሆነ እግዚአብሔር ያስብብናል››
ቅዱስ እንጦስ

አሰግድ ሣህሉ “ተሐድሶ ማለት እኔ ነኝ” አለ


* በስም ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት አባ ሰረቀ ከሀገር ሊወጡ ነው፤

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 5/2011)፦ ወደ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ መዋቅር በመግባት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ዓላማ ለማሳካት ከሚፍጨረጨሩትና ከእነርሱም መካከል እንደ ዋነኛ ከሚታዩት የወቅቱ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቅጥረኞች አንዱ ሆነው አሰግድ ሣህሉ “ተሐድሶ ማለት እኔ ነኝ” ሲል በገዛ አንደበቱ መናገሩ ተሰማ፡፡ አሰግድ ይህን ምስክርነት ስለ ራሱ የሰጠው ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ለንባብ እንደሚበቃ በተጠቆመ አንድ መጽሔት ሰሞኑን በሰጠው ቃለ ምልልስ ነው፤ ንግግሩንም በአንድ ወቅት በ‹ተሐድሶ› ጉዳይ ላይ ለጠየቀችው አንዲት ሴት የመለሰው መሆኑ ተገልጧል፡፡



ግለሰቡ ቃለ ምልልሱን ከሰጠና መጽሔቱ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ማተሚያ ቤት ከገባ በኋላ ይህ ቃሉ ከቃለ ምልልሱ እንዲወጣለት አልያም ቃለ ምልልሱ ጨርሶ እንዲቀር “ደኅንነቶች ናቸው” በሚላቸው ግለሰቦች ዋና አዘጋጁን ማስፈራራቱ ታውቋል፡፡ አሰግድ በተለያዩ አጋጣሚዎች “ደኅንነቶች ናቸው” በሚላቸው ግለሰቦች እያስፈራራ ሕገ ወጥ ፍላጎቱን እንደሚያስፈጽም ያስታወሱት የዜና ምንጮቹ ግለሰቡ ከዚህ መንገዱ እንዲታቀብ ሊገደድ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡







አሰግድ ባለበት የሃይማኖት ችግርና ባቀረበው የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከትምህርት ገበታ ቢያገደውም ታኅሣሥ 27 ቀን 2003 ዓ.ም በኮሌጁ ላይ በመሠረተው ክስ “የኮሌጁ ውሳኔ አግባብ አይደለም” በሚል ሐምሌ ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም ትምህርቱን እየተከታተለ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም ለክሱ በሰጠው ምላሽ፣ “ጉዳዩ የሃይማኖት ክርክርን የያዘ ስለሆነ ፍ/ቤቱ አከራክሮ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የለውም” ሲል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርቧል፡፡ የፍሬ ነገር ክርክሩንም በተመለከተ፣ “ከሳሽ ቤተ ክርስቲያን የማትቀበለውን ትምህርት የሚያራምዱ በመሆናቸው፣ በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት በዚሁ ጉዳይ አቤቱታ ቀርቦባቸው ቤተ ክርስቲያንም ይህን ማረጋገጧ፣ ከሳሽ ያለሰበካቸው በማታለል የቀበና መድኃኔዓለም ሰበካ ጉባኤ አባል ነኝ በማለታቸው ያቀረቡት ማስረጃ በደብሩ አስተዳዳሪ የተሰረዘ በመሆኑ” የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፡፡ ደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባዎችን (http://www.dejeselam.org/2011/02/blog-post_10.html) ማቅረቧ ይታወሳል፡፡



በሌላ በኩል በማኅበረ ቅዱሳን ላይ በየጊዜው በፈጸሙት የስም ማጥፋት ድርጊት ክስ ተመሥርቶባቸውና በማስረጃ ተመስክሮባቸው እንዲከላከሉ ትእዛዝ የተሰጣቸው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ በአቡነ ጳውሎስ ጥያቄ ፍትሕ ሚኒስቴር ክሱ ለጊዜው እንዲቋረጥ ካስደረጉ በኋላ ነገ ቅዳሜ ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን - ዲሲ ለመብረር መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል፡፡ በዋና ሓላፊው ጥብቅ ቁጥጥር ሥር በሚዘጋጀው የመምሪያው ድረ ገጽ ላይ “ክሱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ በነጻ እንደተሰናበቱ” አስመስለው እንዲዘገብ ያደረጉት አባ ሰረቀ ከሕግ የበላይነት ለመሸሽ በጀመሩት መንገድ ከሀገር ለመውጣት መወሰናቸውን ነው ምንጮቹ የጠቆሙት፡፡ አባ ሰረቀ በድረ ገጹ ያወጡት የተሳሳተ ዘገባ እንዲታረም ክሱ ለጊዜው እንዲቋረጥ ባዘዘው በፍትሕ ሚኒስቴር ሰዎች ቢነገራቸውም “እምቢ፣ አይሆንም፣ አልሰርዘውም” አልኳቸው እያሉ በጀብድ መልክ ሲያወሩ መሰንብታቸው ተገልጧል፡፡ የ1200 ዜጎችን ከ56 ሚልዮን ብር በላይ አላግባብ ወስዷል የተባለው የአስካሉካን ትሬዲንጉ ግርማይ ከሕግ ተጠያቂነት መሸሽ እንደማይችል ታውቆ ሰሞኑን በኢንተርፖልና በመንግሥት ጥረት በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል፡፡ የእኛው አባ ሰረቀስ? የፍትሕ ፈላጊ ኦርቶዶክሳውያን ጥያቄ ነው፡፡